የደብረታቦርና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየሸሹ ነው

ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች ተማሪ የላከችልን ምስል እንደሚየሳየው ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በፀጥታ አካላት ተከቧል
አጭር የምስል መግለጫ ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች ተማሪ የላከችልን ምስል እንደሚያሳየው ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በፀጥታ አካላት ተከቧል

በባህርዳር ከተማ ቢቢሲ ያነገጋራቸው የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሰኞ ማታ ጀምሮ ግጭቶችን በመፍራት ግቢውን ለቀው ወጥተዋል።

ከሳምንት በፊት ወልዲያ ከተማ በወልዲያ ስፖርት ክለብ እና በመቀሌ ከተማ መካከል ሊደረግ የነበረው የእግር ኳስ ጨዋታ ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ህይወት የጠፋ ሲሆን ንብረት ላይ ዘረፋና ወድመት ተከስቷል።

ከዚያ በኋላ በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ሰላም እንዳልነበረና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችም ብጥብጥ እንደቀጠለና በተለይም በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ግጭት ጋር ተያይዞም ፍራቻቸው እንደነገሰ እነዚሁ ተማሪዎች ገልፀዋል።

በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲም ሞት ተከስቷል እየተባለ እንደሆነና በዚህም ምክንያት ሸሽተው ወደ ባሕርዳር እንደመጡ ተማሪዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተማሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ መወሰናቸውን ነው የገለፁት ከፊሎቹ ደግሞ ሁኔታውን አይተው ከተረጋጋ ለመመለስ እንዳሰቡ ተናግረዋል።

አጭር የምስል መግለጫ በባህር ዳር ከተማ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሻንጣቸውን ይዘው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በዝግጅት ላይ

በትናንትናውም ዕለት ከሰዓት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ከሽማግሌዎች ጋር ተማሪዎቹን ሰብስበው ሰኞ ፈተና እንደሚኖርና የቤተ-መፃህፍትና ሌሎች አገልግሎቶችም እንደሚኖሩ ገልፀውላቸዋል።

በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የፀጥታ ኃይሎችም እንደገቡ እነዚሁ ተማሪዎች ተናግረዋል።

በአክሱም፣ ሃሮማያና ወልዲያ ያሉ ጓደኞቻቸውም ጋር ደውለው ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ነግረዋቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዳይገቡ እንዳይወጡ ተከልክለዋል ጋዜጠኞችም መግባት አይችሉም መባሉን ቢቢሲ ለማጣራት ችሏል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ዘንዘልማ ካምፓስ የፀጥታ ኃይሎች ግቢው ውስጥ እየተንቀሳሱ መሆኑን ቢቢሲ ማረጋገጥ የቻለ ሲሆን አንዳንድ ተማሪዎችም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሲንቀሳቀሱ አይተዋል።