የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ማዕቀቡን ለማስነሳት እሰራለሁ አሉ

አዲሱ የዚምባብዌ ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ Image copyright Reuters

የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት በእጅጉ እየጎዱ በመሆናቸው ምክንያት ሊነሱ ይገባቸዋል ያሏቸውን በምዕራባውያን የተጣሉ ማዕቀቦች ለማስነሳት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አዲሱ የዚምባብዌ ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ተናግረዋል።

በቀጣዩ ዓመት ወርሃ ሐምሌ ላይ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የሃገሪቱ ጠቅላላ ምርጫም ቀደም ብሎ ሊካሄድ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል ፕሬዚዳንቱ።

በዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ጉባዔ ላይ የተገኙት ምናንጋግዋ ምርጫውን ፍትሃዊ፤ ነፃ እና ተዓማኒ ለማድረግ ሁሉን ነገር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ባለፈው ወር ሙጋቤን ተክተው መንበረ ሥልጣኑን የያዙት ምናንጋግዋ ፓርቲያቸውን ወክለው ለሚቀጥለው ዓመት ምርጫ እንደሚወዳደሩ ይጠበቃል።

"ምርጫው ከምታስቡት በላይ ቅርብ ነው" የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ከሕዝብ ዓይን የራቁት የ93 ዓመቱ ሙጋቤ ለጤና ምርመራ ወደ ሲንጋፖር ማቅናታቸውን የሙጋቤ ቃል አቀባይ ጆርጅ ቻራምባ ተናግረዋል።

Image copyright AFP

አሜሪካ የዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ሌሎች ሰዎች ላይ የጣለችው በነፃ የመንቀሳቀስ መብትን የሚያግደው ማዕቀብ ዚምባብዌ ከተጣሉት ቅጣቶች አንዱ ነው።

ትራምፕ ማዕቀቡ በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጥ ካልመጣ በቀር እንደማይነሳ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

"ከሌሎች ሃገራት ተነጥለን የትም ልንደርስ አንችልም፤ ከአጋሮቻችን ጋር በአንድነት ከሠራን የበለጠ ጥቅም እንደምናገኝ እሙን ነው" ሲሉ ተደምጠዋል ምናንጋግዋ።

አልፎም የአውሮፓ ሕብረት ሙጋቤና ባለቤታቸው ግሬስ ላይ ማዕቀብ ከመጣሉም በላይ የሃገሪቱ ጦርና መሰል ተቋማት ላይ እገዳ ማስተላለፉም የሚታወስ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች