ናይጀሪያዊቷ ልጆቿን ልትሸጥ ስትል ተያዘች

የናይጀሪያ ፖሊስ ኃይል Image copyright Getty Images

ናይጀሪያዊቷ እናት የአንድ ወር ዕድሜ ያላቸውን መንታ ሴት ልጆቿን ልትሸጥ ስትል ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏታል።

ህፃናትን በህገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር የተከሰሰች ሲሆን ሌሎችም ክሶች እንደሚጨመሩባት ፖሊስ አስታውቋል።

የተያዘችውም ልጆቿን 27 000 ብር ለመሸጥ ስትደራደር ነው ገዢው ለፖሊስ ያስታወቀው

ህፃናትን መሸጥ እንዲሁም በህገወጥ መንገድ ለጉዲፈቻ መስጠትም ሆነ ማዘዋወር በናይጀሪያ ስር የሰደደ ችግር ነው።

የ30 ዓመቷ እናት በሰሜናዊ ናይጀሪያ በምትገኘው ካትሲና ፍርድ ቤት በቀረበችበት ወቅት ይግባኝ ባትጠይቅም የእምነት የክህደት ቃሏን በሰጠችበት ወቅት ግን "ኢኮኖሚያዊ ችግሮች" እንዳስገደዷት የሀገሪቱ ጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል።

ናይጀሪያ ከፍተኛ የነዳጅ አምራችና ላኪ ብትሆንም አሁንም ብዙዎች በድህነት የሚማቅቁባት ናት።

ዘ ናሺናል ኤጀንሲ ፎር ዘ ፕሮሂቢሽን ኦፍ ትራፊኪንግ ኢን ፐርሰንስ የተሰኘው ድርጅት በአውሮፓውያኑ 2011 ባደረገው ምርመራ ህፃናት እስከ 6500 ዶላር እየተሸጡ እንደሆነ ዘግቧል።

በአውሮፓውያኑ 2013ም 17 እርጉዝ ታዳጊ ህፃናት "የልጆች ማምረቻ ፋብሪካ" ውስጥ እንዳዳነ ፖሊስ ተናግሯል።

ምንም እንኳን የህዝብ ተቃውሞም ሆነ መንግሥት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቁጥጥር ቢያደርግም ልጆቻቸውን የሚሸጡ እናቶች ቁጥር ቀላል አይደለም።

የ"ህፃናት ማምረቻ ፋብሪካው"ቅሌት ከተጋለጠ በኋላ ሌላም አንዲት እናት ሴት ልጇን በ90 ዶላር ስትሸጥ ተይዛለች።

ተያያዥ ርዕሶች