ቀጣዩን የኤኤንሲ መሪ ለመምረጥ ሩጫ

ሁለቱ ተወዳዳሪዎች ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማና ሲሪል ራማፎዛ Image copyright Reuters/AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሁለቱ ተወዳዳሪዎች ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማና ሲሪል ራማፎዛ

የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ የሆነው የአፍሪካዊያን ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ፕሬዝዳንት የሆኑትን ጃኮብ ዙማን በፓርቲው መሪነት የሚተኩ ሁለት ተወዳዳሪዎች ታውቀዋል።

እነሱም ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛና የቀድሞው ካቢኔ ሚኒስትር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ማለትም የፕሬዝዳንት ዙማ የቀድሞው ባለቤት ናቸው።

ለሌሎች አምስት የፓረቲ የሥልጣን ቦታዎች የተሰየሙ ተወዳዳሪዎችም አሉ።

በምርጫው ዙሪያ የነበሯቸውን ቅሬታዎች ስሜታዊ በሆነ መንገድ ጩኸት በተሞላበት መልኩ ያንፀባረቁ ልዑካን ነበሩ።

ለመሪነት ቦታው የሚደረገው ፉክክር የተጋጋለ ፖለቲካዊ ፍትጊያን በማስከተሉ በመጪው ዓመት ከሚከናወነው ምርጫ በፊት ፓረቲው ለሁለት እንዳይከፈል የሚል ፍራቻን አሳድሯል።

ፕሬዝዳንት ዙማም ቢሆኑ ፓረቲው አደጋ ላይ እንደሆነ ''መስቀለኛ መንገድ ነው'' በማለት አስጠንቅቀዋል።

በኔልሰን ማንዴላ ሥር ሃገሪቷ ዲሞክራሲን ስትቀበል ጀምሮ ኤኤንሲ ሥልጣን ላይ ቆይቷል። በጆሃንዝበርግ በተካሄደው የአራት ቀናት የፓርቲው የምርጫ ኮንፈረንስ ላይ ከ5ሺህ በላይ ልዑካን ተሳታፊ ሆነዋል።

ለቢቢሲ ጋዜጠኛዋ ሌቦ ዲስኮ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙ እንደነገሯት ውጤቱ ይፋ ሲደረግ በማሸነፍና በመሸነፍ መካከል የሚኖረው ልዩነት ትንሽ እንደሚሆን ነው።

የአመራሩ ምርጫ በምስጢር ዝግ በሆነ መልኩ ስለተካሄደ ሕጋዊ ጥያቄዎች ሊያስከትል እንደሚችል ይታሰባል። ውጤቱ እሁድ ዕለት ይታወቃል ተብሎ ቀድሞ ተነግሮ ነበር።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ልዑካኑ የተጣሉበት የምርጫው ሂደት ክፍፍል ይንጸባረቅበት ነበር

የምርጫው ሂደት ተገቢ ውክልና የሌላቸው ልዑካን እውቅና ሲያገኙ እውነተኛ ልዑካን ደግሞ ተከልክለው የሚለው ውዝግብ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ ዘግይቶ ነበር።

እ.አ.አ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በሥልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዚዳንት ዙማ ብሔራዊ ምርጫ እስከሚካሄድበት እ.አ.አ እስከ 2019 ድረስም በሥልጣን ላይ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ደቡብ አፍሪካ ለፕሬዝዳንት ሥልጣን ሁለት የአምስት ዓመት ገደብ አስቀምጣለች።

የ75 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ዙማ በኤኤንሲ ፓርቲ ዙሪያ ባሉት በርካታ ውዝግቦች ዋና ርዕስ ናቸው። ከዚህ ቀደም በሥልጣን እያሉ በፓርላማ መተማመኛ ድምጽ ተሰጥቶባቸው ሥልጣን ነበር። በአሁን ሰዓት ደግሞ እሳቸው የሚያስተባብሏቸው በርካታ ብዙ የሙስና ክስ ይቀርብባቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ የቀድሞ ባለቤታቸው ለሆኑት ድላሚኒ ዙማ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። የ68 ዓመቷ ድላሚኒ ዙማ የረጅም ዘመን ፖለቲከኛ ሲሆኑ በሃገሪቱ ያሉ በነጮች የተያዙ ንግዶችን ሲቃወሙ ቆይተዋል። አራት ልጆችን ቢወልዱም ከተፋቱ 20 ዓመት ገደማ ሊሆናቸው ነው።

የኤኤንሲ የሴቶች ክንፍ ቀድሞ መሪ የነበሩት ድላሚኒ ዙማ ለደቡብ አፍሪካ መንግሥት የውጪ ጉዳይ፣ የቤትና የጤና ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

የድላሚኒ ዙማ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳ ከዋና ተቃዋሚያቸው ባለሃብቱ የቀድሞ የሠራተኞች መሪ ከነበሩት የአሁኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ የተለየ ነው።

የ65 ዓመቱ ራማፎዛ በሙስና ላይ ያላቸውን ጥብቅ አቋም ያሳወቁ ሲሆን የንግድ ማህበረሰቡም ድጋፍ አላቸው።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የምርጫው ውጤት ሌላ ቢሆንም ፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማ እ.አ.አ 2019 ድረስ በሥልጣን ይቀጥላሉ

ባላፈው ቅዳሜ እንደ ፓርቲ መሪ የመጨረሻ የሆነውን የኮንፈረንሱ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ ፕሬዚዳንት ዙማ የተፈጠረውን የአመራር ሽኩቻ አስመልክቶ 'አሳፋሪ ጭቅጭቅ' በማለት ቁጣቸውን ገልፀዋል።

ባለፈው ዓመት በተደረጉት የአካባቢ ምርጫ ላይ ኤኤንሲ ባስመዘገበው ውጤት ዙሪያ ''ይህ ውጤት ኤኤንሲን በተመለከተ ሕዝባችን ደስተኛ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው'' በማለት ፕሬዚዳንቱ ተናግረው ነበር።

በዚህ ንግግር ላይ 'ሌብነትና ሙስና' በመንግሥትም ዘርፎች እንዳለ ሁሉ በግሉም ዘርፍ እንዳለ በእርግጠኝነት ሲገልፁ፤ በተጨማሪም ''ጥቁር ሆኖ ስኬታማ የሆነ ሰው በሙስና እንደሆነ ይታሰባል'' በማለት ተናግረዋል።

የሃገሪቱን ሚዲያ 'ኢፍትሐዊና የሚያዳላ' ነው በማለት ቁጣቸውንም ገልጸዋል። የሃገሪቱን የፍትሕ ሥርዓትም ዒላማ በማድረግ በፓርቲው ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ መግባት እንደሌለበት አሳስበዋል።

በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በነጮች ትመራ የነበረቸው ሃገር በምርጫ ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ ፓርቲው በሚገርም ሁኔታ ሁሉንም ምርጫ እያሸነፈ መጥቷል። ባለፈው ዓመት በተደረገው ምርጫ ግን ኤኤንሲ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ አስመዝግቦ የማያውቀውን ዝቅተኛ የተባለውን የ54% ውጤት አግኝቷል።

የቢቢሲው አንድሩው ሐርዲንግ እንዳለው ጥያቄው ኤኤንሲ በከፋ ውድቀት ውስጥ ከሆነ ይህ የደቡብ አፍሪካን መረጋጋትና የወደፊት ዕጣ ፈንታን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል ብሏል።

ተያያዥ ርዕሶች