ለቤተሰብ ምግብ ወይስ ለህክምና ይክፈሉ?

Aerial shot of Olive Link clinic

ለቤተሰብ ምግብ፣ ለህፃናት ህክምና፣ ልጆች መፀዳጃ ቤት መጠቀም እንዲችሉ ከመክፈልና መሰል ጉዳዮች የቱን ላድርገው ለየቱ ላውጣ ብሎ መጨነቅ በኬንያ ያሉ የድሆች መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ በርካታ እናቶች እጣ ነው።

ፒስ፤ የሱሳን ምቡላና ባለቤቷ አራተኛ ልጅ ነች። እነ ሱሳን የሚኖሩት ሲናይ የሚባል የናይሮቢ የተጨናነቀ መንደር ውስጥ ነው። መኖሪያ ቤታቸው አንድ ክፍል ሲሆን በአንድ አግዳሚ ሶፋ ከፍለውተል። ከጎረቤቶቻቸው ጋር ሲነፃፀር የነሱሳን ቤት ጥሩ የሚባል ነው።

የተጨናነቀው የነሱሳን መንደር ውሃ የለውም። የንፅህና አገልግሎትም ብርቅ ነው። በየቤቱ ውሃ ማግኘት የዕለት ከዕለት ትልቁ ጉዳይ ነው። ህክምና ደግሞ ቅንጦት ነው።

ሃያ አምስት በመቶ የሚሆኑ ኬንያዊያን የሆነ አይነት የጤና መድህን ሽፋን አላቸው። ቀሪዎቹ ግን ወደ ሃኪም ቤት ሲሄዱ የሚከፍሉ ናቸው። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ለድህነት እንደዳረገ የኬንያ ጤና ጥበቃ ፌደሬሽን ይገልፃል።

ለብዙዎች ለጤና ሽፋን መቆጠብ፣ ወይም ቅድመ ክፍያ የሚቻል አይደልም።

እድሜ ለሱሳን የሞባይል የጤና ሽፋን ይሁንና ፒስ መከተብ የቻለች የሱሳን ብቸኛ ልጅ ነች።

"በሌሎቹ ልጆቼ ጊዜ ከባድ የገንዘብ ችግር ነበረብኝ። ለህክምና ምንም መክፈል አልችልም ነበር" በማለት ታስታውሳለች ሱሳን።

"የቅድመ ወሊድ ክትትልና የተለያዩ ምርመራዎችን ለማድረግ ወደ ክሊኒክ መሄድ አልችልም ነበር። በፒስ እርግዝና ጊዜ ግን በሞባይል ቁጠባዬ አማካኝነት ክሊኒክ መሄድ ችያለሁ"ትላለች።

ኬንያ ውስጥ ኤም-ፔሳ የሚባል በሞባይል ክፍያ መፈፀም የሚያስችል ሥርዓት አለ። ኤም-ፔሳ 19 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት። ሱሳን ተጠቃሚ የሆነችበት የጤና ሽፋን ኤም-ቲባ ደግሞ በኤም-ፔሳ ስር የሚሰራ ነው።

ብዙ ኬንያዊያን ድንገተኛ የጤና ችግር ሲያጋጥማቸው ከጓደኞቻቸውና ከዘመዶቻቸው ገንዘብ ያሰባስባሉ፤ አልያም ያላቸውን ንብረት እንደሚሸጡ የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስኪያጅ ቦብ ኮሊሞር ይናገራሉ።

"ስለዚህ የኤም-ቲባ ተጠቃሚዎች ትንሽ ገንዘብ ቆጥበው ለጤና ሽፋን ብቻ እንዲጠቀሙ እድል ሰጥቷል" ይላሉ ኮሊሙር። ይህ ብቻም ሳይሆን ተጠቃሚዎች ለሌሎች የጤና ሽፋን ይውል ዘንድ ገንዘብ ማስተላለፍ ይችላሉ።

"መጀመሪያ እዚህ ሥርዓት ውስጥ ስገባ በጣም ተጠራጥሬ ነበር። ደጋግሜ ሂሳቤን እመለከት ነበር። በመጨረሻ ግን ገንዘቤ እንዳለና ቁጠባዬ እንደቀጠለ አየሁ" ትላለች ሱሳን።

አንዱ ከአንዱ እየሰማ አሁን በሲናይ የተጨናነቁ መንደሮች ብዙዎች የኤም-ቲባ ተጠቃሚ ሆነዋል። የኤም-ቲባ አካሄድን በተመለከተ የኬንያ የህክምና ባለሙያዎች ቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር ኔሊ ቦሲር ለቢቢሲ "ምናልባትም ይህ ሀምሳ በመቶ ለሚሆነው ህዝባችን የሚያዋጣ መንገድ ነው" ብለዋል።

ነገር ግን ብቸኛው መንገድ ነው አይሉም። ቢሆንም ግን ጤና ለሁሉም ሽፋን ላይ ለመድረስ ዓይነተኛ መንገድ ነውም ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ዘዴ ጤና ነክ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንደሚጠቅም ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት በዚህ መልኩ የተደራጀ መረጃ መግኘት ተችሏል። መረጃዎቹ የሰዎችን ህክምና የማግኘት ልማድ፣ ለምሳሌ ወባን ለማከም ምን ያህል ይፈጃል የሚሉና መሰል መረጃዎች እነደሚገኙ ተጠቁሟል።

ይህ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማቀድና ፖሊሲ ለማውጣት እንዲሁም የተለያዩ የጤና ጉዳዮችን በተሻለ ለመመለከት ያስችላል።

ሁለት ዓመት ከማይሞላ ጊዜ በፊት ኪብራ ከሚባለው የናይሮቢ የተጨናነቀ መንደር ከኤም-ቲባ ጋር የሚሰራው አንድ ክሊኒክ ብቻ ነበር። አሁን ግን በመሰል የተጨናነቁ መንደሮች የሚገኙ 549 ክሊኒኮች ከኤም-ቲባ ጋር እየሰሩ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ሱሳን ያሉ ድሆች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።

ተያያዥ ርዕሶች