የመሬት ይዞታ ውዝግብን የሚያስቀር አዲስ ዘዴ

Family in farmyard Image copyright Landmapp

ግብርና በራሱ እጅግ አድካሚ የሆነ ሥራ ነው። የሚያርሱት መሬት የእርስዎ አይደለም መባል፤ ይህን ማረጋገጠ አለመቻል ደግሞ ከዚህም በላይ የከፋ ነው።

ለምሳሌ በጋና አስር በመቶ የሚሆኑ ትንሽ መሬት ያላቸው ገበሬዎች ብቻ ናቸው መሬታቸው የራሳቸው ለመሆኑ የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው። ይህ ደግሞ አስቸጋሪ ከመሆኑ ባሻገር ግጭት ውስጥም ሊከታቸው ይችላል።

በዚህም ሳቢያ ለገበሬዎቹ መሬታቸው ብቸኛ ሃብታቸው ቢሆን ይህን መሬት አስይዘው እንኳ መበደር አይችሉም። ስለዚህም ላንድማፕ የተሰኘ ኩባንያ ለዚህ መፍትሄ ይዞ ብቅ ብሏል።

ይህ በሞባይል ጂፒኤስ (የቦታ ተቋሚ) በመጠቀም አነስተኛ ገበሬዎች የመሬት ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ያስችላል። በዚህ ገበሬዎች የመሬታቸው ፕላንና የባለቤትነት ማረጋገጫ ይሰጣቸዋል።

"የመሬት ባለቤትነት አለመረጋገጥ ለግብርና ኢንቨስትመንት ትልቅ እንቅፋት ነው"ይላሉ የላንድማፕ ዋና ሥራ አስኪያጅና የቴክኒክ ሃላፊ ።

የመሬት ባለቤትነት በማስረጃ ካልተረጋገጠ መብትን የሚያሳጣ እንደሆነና ገበሬውም በማስያዣነትና በዋስታና ሊጠቀም የሚችለው በዚህ ማስረጃ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ።

ጥሩ ውሎች

ግጭቶች በገበሬዎች መካከል ብቻም ሳይሆን በገበሬዎችና ምርታቸውን በሚገዟቸው ኩባንያዎች መካከልም ይከሰታሉ።

አብዛኛውን ጊዜ በገበሬዎችና በእነዚህ ኩባንያዎች መካከል የሚደረግ ስምምነትና ውል መተማመንን መሰረት ያደረገ ነው።

Image copyright Getty Images

ማስረከብ ያለባቸውን ያህል ምርት አላቀረቡም በሚል አምራች ገበሬዎች ክፍያቸውን ሳያገኙ የሚቀሩበት ጊዜም ጥቂት አይደለም።

ይህን ታሳቢ በማድረግ ፍሬሽማርት የተሰኘ ሌላ ኩባንያ ደግሞ አምራች ገበሬዎችና ምርት ገዥ ኩባንያዎች ዲጂታል ስምምነቶችን እንዲያደርጉ የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) ፈጥሯል።

መተግበሪያው የመሬት ይዞታን፣ የሰብል ሁኔታን እንዲሁም የምርት ገበያን የሚመለከት መረጃን ሁሉ አቀናጅቶ የያዘ ነው። ይህ ደግሞ ምን ያህል ሰብል በምን ያህል ጉልበት ተመርቷል የሚለውንም ትንታኔ በማስቀመጥ ለምርት የሚሰጥ ዋጋን ለማስላት ያስችላል።

ከምርት ትራንስፖርት እንዲሁም አስተሻሸግ ጋር በተያያዘም መረጃ ማግኘት ይቻላል። በዚህ የሚመለከታቸው ሁሉ ሊጠቀሙ ይችላሉ።

እነዚህ ነገሮች የሚያሳዩት የገበሬውን ችግር በተራቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሳይሆን በቀላል ዘዴዎች መፍታት እንደሚገባ ነው። በዚህ መልኩ የገበያ ትስስር፣ የአየር ሁኔታ ትንበያን የመሰሉ መረጃዎችንም ማግኘት ይቻላል።

እስከዛሬ ገበሬዎች ከመንግሥት ባለሙያዎች በሚገኝ መረጃ ላይ ተመስርተው ነበር እንቅስቃሴያቸውን የሚያደርጉት። ባለሙያዎቹ ገበሬዎችን የሚጎበኙት ደግሞ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ ስለሚሆን ይህ ጊዜ ደግሞ ብዙ ችግር ሊፈጠር የሚችልበት ሊሆን ይችላል።

አሁን ኩባንያው በዘረጋው ሥርዓት ግን ገበሬዎች ዕለት ከዕለት መረጃ ማግኘትና ያሻቸውን መወሰን ይችላሉ።

ቴክኖሎጂው ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመፍታት፣ የገበያ ትስስር በመፍጠርና የተሻሉ ምርቶችን ከመዝራትና መሰል ነገሮች ጋር በተያያዘ የተለያዩ እድሎችን ከፍቷል።

ይህ ቀላል ነገር ቢመስልም ትልቅ ችግር መፍታት ያስቻለ እርምጃ ነው። ለአነስተኛ ገበሬዎች የገንዘብ ብድርና ድጋፍ አገልግሎቶችን ማመቻቸት የቴክኖሎጂ ተኮር ፈጠራዎች ትኩረት መሆን አለበትም ተብሏል።

ዘጠና በመቶ የሚሆነውን የአፍሪካን የግብርና ምርት የሚያመርቱት 33 ሚሊዮን የሚሆኑ አነስተኛ አምራች ገበሬዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

ስለዚህም እነዚህ ገበሬዎች ሀብት እንዲፈጥሩና ከገቢ አንፃር ጠንካራ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ይታመናል።

ከሞላ ጎደል ከሰሃራ በታች የሚገኝ ሁለት ሦስተኛው ሕዝብ በቀን ከ1.25 ዶላር በታች የሚያገኝ ነው።

ስለዚህ ርካሽ ስማርት ስልኮች ብድር ለማግኘት፣ ለቁጠባ፣ ለኢነቨስትመንትና ለሌሎችም ነገሮች ለገበሬው አይነተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል ማለት ነው።

በርግጥም ነፃ ኢንተርኔት ማግኘት ለገበሬው ትልቅ ጠቀሜታ አለው መንግሥታት ከዚህ አንፃር ሊሰሩም ይገባል ይላሉ ባለሙያዎች።