ዛምቢያ ቻይናዊ ፖሊሶችን የመቅጠር ዕቅዷን ሰረዘች

ዛምቢያ ቻይናውያንን ፖሊስ አድርጋ ቀጠረች Image copyright MWEBANTU MEDIA

የዛምቢያ ፖሊስ ኃይል ስምንት ቻይናዊያንን በፖሊስነት ሊቀጥር መሆኑን ካሳወቀ ከ24 ሠዓታት በኋላ ከሃገሪቱ ዜጎች በገጠመው ተቃውሞ ዕቅዱን ሰርዞታል።

አዲሶቹ ቻይናዊያን ቅጥር ፖሊሶች በሃገሪቱ ዋና ከተማ ሉሳካ ውስጥ እንዲያገለግሉ ሰኞ እለት ነበር የተቀጠሩት።

ነገር ግን ውሳኔው ሕዝባዊ ቁጣን በመቀስቀሱ፤ በተለይ ደግሞ በዚህ ዓመት የሃገሪቱ ፖሊስ መኮንኖች 'ለደህንነት' ሲባል የውጪ ዜጎችን እንዳያገቡ የሚያግድ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ መሆኑ የበለጠ ተቃውሞውን አባብሶታል።

በተጨማሪም ጥምር ዜግነት ያላቸው ዛምቢያዊያን ጭምር በሃገሪቱ ፖሊስ ኃይል ውስጥ እንዳይቀጠሩ ተከልክለዋል።

የፕሬዝደንቱ ቃል-አቀባይ የነበሩት ጠበቃው ዲክሰን ጄሬ እንዳሉት በጉዳዩ ላይ የሃገሪቱ ሕገ-መንግሥት አሻሚ ነገር የለውም።

"የራስህ ዜጎች ጥምር ዜግነት ስላላቸው በፖሊስነት እንዳይቀጠሩ እየከለከልክ፤ ከሃገሪቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ቻይናዊያን ግን የፖሊስ አባላት እንዲሆኑ የምትፈቅድ ከሆነ ቆም ብለህ እንድታስብ ያስገድዳል'' ሲሉ ጠበቃው ተናግረዋል።

በዛምቢያ የቻይናውያን ፖሊሶች ቅጥር ብዙዎች በአግራሞት ራሳቸውን እንዲነቀንቁ ያደረገ ሲሆን በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ የዛምቢያ መንግሥት የሌላ ሃገር ዜጎች በደህንነት ሥራ እንዳይሰማሩ በቅርቡ እገዳ መጣሉ ነው።

ይህ የመንግሥት እርምጃ የውጭ ጣልቃ ገብነት ላሳሰባቸው ሰዎች እፎይታን ለግሶ እንደነበር አይዘነጋም።

የመንግሥት የአሁኑ እርምጃ ግን ዛምቢያውያን በሃገሪቱ የሚገኙ ከ20 ሺህ በላይ የሚገመቱ ቻይናውያንን በጥርጣሬ እንዲመለከቱ እያደረጋቸው ነው።

የትርፍ ጊዜ የፖሊስ መኮንኖቹ በዛምቢያ ከቻይና ማሕበረሰብ ጋር የተያያዘ ምንም ዓይነት ሥራ ይሠራሉ ተብሎ ግን አይጠበቀም።

የፖሊስ ቃል-አቀባይ ኢስተር ካቶንጎ እንዳሉት የቻይናውያኑ ፖሊሶች ሥራ የሚሆነው ለመደበኛ መኮንኖች እርዳታ ማድረግ ብቻ ነው።

"በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ ህንዳውያን ነበሩ፤ ማንም ስለነሱ ምንም አላለም። የቻይናውያኑ እንዲህ መነጋገሪያ መሆንና መገለል አልገባኝም" ሲሉ ይጠይቃሉ።

ተቃውሞዎች የበረቱበት የዛምቢያ ፖሊስ ምንም እንኳ የቻይናውያኑ ቅጥር ሕግ የጣሰ ባይሆንም በአቋሙ መፅናት ግን አልቻለም።

ተያያዥ ርዕሶች