የኢንተርኔት ገበያ በሶማሊያ

From left to right Abdiqani Ibrahim, Hamse Musa and Saed Mohamed Image copyright Innovate Ventures

ሰኢድ ሞሃመድ በኢንተርኔት ለመገበያየት የሚያስችለውን ሙራድሶ የተሰኘውን ድረ-ገፅ ሰርቶ እንደ አውሮፓውያኑ 2015 ላይ በምሥራቅ አፍሪካ የንግድ ውድድር ላይ ተሳተፈ።

ነገሮች ጥሩ አልነበሩም። ተቀባይነት እንደማያገኝ ተሰምቶት ነበር። እንደፈራውም የንግድ ሃሳቡ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ።

ወድድሩን ይገመግሙ የነበሩት አብዲጋኒ ዲሪዬ በሞሃመድ የንግድ ውድድረ ሃሳብ ደስተኛ እንዳልነበሩ ይናገራሉ። "ከኢንተርኔት ግብይት ጋር በተያያዘ የቀረቡ ሃሳቦች ውስን ነበሩ በእነሱም ደስተኛ አልነበርንም'' በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሞሃመድና ጓደኛቹ ግን በዚህ ተስፋ አልቆረጡም።

ሞሃመድ እንደሚለው ደግሞ ከዚህም በኋላ ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ምላሾች ተሰጥተዋቸዋል። እነሱ ግን አይሆንምን እንደ መልስ መቼም ተቀብለው አያውቁም።

በመጨረሻም በዚያው የንግድ ሃሳባቸው በተጣጣለበት ውድድር ላይ በመሳተፍ ሊያሸንፉ ችለዋል።

"የሚያስደንቀው ከሌሎቹ የንግድ ሃሳቦች የእነሱ በጣም ስኬታማ መሆኑ ነው" በማለት መጀመሪያ የንግድ ሃሳቡን ያጣጣሉት ዲሪዬ ይናገራሉ።

በርግጥ የድረ-ገፅ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ላይ ብቻ ያተኮረው የእነሞሀመድ የንግድ ሃሳብ መጀመሪያ ላይ ስኬታማ መሆን አልቻለም ነበር።

ምክንያቱም ሶማሊያ ለዚህ የድረ-ገፅ የኢንተርኔት ገበያ ዝግጁ አልነበረችምና። ከ 14 ሚሊዮን ህዝቧ ሦስት በመቶ የማይሞላው ኢንተርኔት በሚያገኝበት፤ ጥቂቶች ብቻ የባንክ ሂሳብ ባለቤት በሆኑባት ሶማሊያ ይህ የሚያስደንቅ አይደለም።

ስለዚህ እነሞሃመድ የምዕራብ አገራት ነጋዴዎችን የማሳተፍ መላ ዘየዱ። በዚህ መልኩ የአማዞንና የዋልማርትን ልምድን በማጤን እርምጃቸውን ማስተካከል ጀመሩ።

በዚህም ውጤታማ መሆን ቻሉ። ከዚያም የእነሞሃመድ 'ሙረድ'ሶ ስኬት በስኬት ሆነ። ኤሌክትሮኒክስ ላይ ብቻ ማተኮሩን ትቶ ሌሎችንም ነገሮች በመጨመር ክፍያውንም በኢንተርኔት ብቻ ሳይሆን በጥሬ ገንዘብም እንዲሆን በማድረግ ለገበያተኛው የክፍያ ነፃነት ሰጡ።

በሶማሊያ ብሎም በአጠቃላይ አፍሪካ የኢንተርኔት ግብይት ገና በጅማሮ ላይ ነው የሚሉት ኦቨም የተባለ ጥናት ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ማቲው ሪድ ናቸው።

Image copyright Getty Images

"በርካታ ሰዎች በአነስተኛ ገቢ በመኖር ላይ ናቸው። የኢንተርኔት ገበያ ደግሞ መካከለኛ ገቢ ላላቸው ነው። ስለዚህ ይህ ለኢንተርኔት ገበያ ትልቅ ተግዳሮት ነው" ይላሉ።

ተግዳሮት ከሚሏቸው የመሰረተ-ልማት በተለይም የቴሌኮም አገልግሎት ችግር ቀዳሚው ነው። ቢሆንም ግን ነገሮች እየተሻሻሉ መሆኑን አይክዱም።

ለዚህ ዋነኛ ማሳያ የሚሆነው ሚሊዮኖች በአፍሪካ የመስመር ስልክን አልፈው ሞባይል ወደ መጠቀም የተሸጋገሩ መሆኑ ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 በአፍሪካ የሞባይል ተጠቃሚ 725 ሚሊዮን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ደግሞ ሶማሊያ ትልቅ ተጠቃሚ ትሆናለች ተብሎ ይታመናል።

"በአፍሪካ ሞባይል በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው ይህ ደግሞ ብዙ እድሎችን ይፈጥራል። እንደ ሞባይል ያሉ ነገሮችም ብዙዎች በቀላሉ የሚገዟቸው ሆነዋል" ይላሉ ሪድ።

እሳቸው እንደሚሉት የማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች እየተቀየሩ መሆን፣ የወጣት ቁጥር እየጨመረ መምጣት እንዲሁም የከተሞች መስፋፋት ለኢንተርኔት ገበያ ምቹ ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት ደቡብ አፍሪካ የተጠናከረ የኢንተርኔት ግብይት ሥርዓት ያላት ሲሆን ኬንያና ናይጄሪያም ተጠቃሚዎችን እያገኙ ነው። ለምሳሌ ጁሚያ የተሰኘው የድረ-ገፅ መደብር በሦስቱም አገራት ይንቀሳቀሳል።

የአማዞንን ልምድ ሙሉ በሙሉ መቅዳት ሳይሆን ከአፍሪካ እውነታ በመነሳት ነገሮችን ማጣታም እንደሚያስፈልግ ዲሪዬ ይናገራሉ።

ጁሚያን በምሳሌነት በመጥቀስ ደንበኞች ገንዘባቸውን ከማውጣታቸው በፊት የሚያገኙት ጥቅም መኖሩን ማሳየት መቻሉ ትልቅ ነገር እንደሆነ ይናገራሉ።

በተቃራኒው ሙራድሶ ገና ትንሽ ሲሆን ወርሃዊ ሽያጩም በወር እስከ አርባ ሺህ ዶላር የሚሆን ሳሚኦንላየን የተሰኘ ተወዳዳሪም መትቶበታል። ሌሎች ተወዳዳሪዎችም እንደሚመጡ ዲሪዬ ይናገራሉ።

ይህ ደግሞ ለሶማሊያ ህዝብ ጥራት ያለው እቃ ማግኘት ብቻም ሳይሆን ምርጫ መስፋትም ትልቅ ሚና አለው።

"በሶማሊያ ስማርት ፎኖች እየረከሱ በመሆኑ ብዙዎች ስልኮቹን መያዝ ችለዋል። የኢንተርኔት ግብይት ደግሞ እቃ ለመግዛት ከከተማ ከተማ መሄድን አስቀርቶላቸዋል" በማለት፤ ይህ ደግሞ ጊዜና ገንዘባቸውንም ለመቆጠብ እንደሚጠቅም ዲሪዬ ይናገራሉ።