ዜግነት ለመግዛት ምን ያህል ይከፍላሉ?

አማር አልሳዲ

የመናዊቷ አማር አል ሳዲ ማልታ ከቦምብ ፍንዳታና ከአሰቃቂ በሽታዎች እንዳዳነቻት ትናገራለች።ቤተሰቦቿም በጦርነት የምትታመሰው የመንን የለቀቁት በተባበሩት መንግሥታት እርዳታ ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር።

"ዓለም ላይ ማንም በዚያ መልኩ መኖር አይፈልግም።አንድ ቀን ሁላችንም ተኝተን ከፍተኛ የቦምብ ድምፅ ቀሰቀሰን።በጣም የሚያስደነግጥ ድምፅ ነበር።"የምትለው አማር ጓደኞቿ አሁንም በየመን እንደሚገኙ ትናገራለች።

ጓደኞቿ ዛሬም በየመን ሰዎች በኮሌራ በሽታ እየሞቱ እንደሆነ ነግረዋታል።የተወሰኑት ከሃገር ለመውጣት ቢሞክሩም ማንም ፓስፖርታቸውን ሊቀበለው ስላልቻለ ፍላጎታቸው አልተሳካም።

አማር፣ወላጆቿና ሌሎች አራት ልጆቻቸው የማልታ ስደተኞች አይደሉም።ይልቁንም የማልታ ዜጎች ናቸው።

ነገር ግን የተወለዱት ማልታ ውስጥ አይደለም፣ የማልታ ዜግነት ያለው ዘመድም የላቸውም። ታዲያ እነ አማር እንዴት የማልታ ፓስፖርት አግኝተው ዜጋ ሊሆኑ ቻሉ?

ይህ ሊሆን የቻለው እነ አማር የማልታ ፓስፖርት መግዛት በመቻላቸው ነው።ማልታ እንደ አውሮፓውያኑ 2014 ላይ ፓስፖርት መሸጥ መጀመሯን ተከትሎ እንደ ብዙ ስደተኞች እነ አማርም ፓስፖርት በመግዛት የማልታ ዜጎች መሆን ችለዋል።

የፓስፖርቱ ገበያ

እንግሊዝን ጨምሮ በርካታ ሃገራት ለውጭ ዜጎች የኢንቨስትመንት ቪዛ እንደሚሰጡ ሁሉ ማልታም ለግለሰብ ነጋዴዎች ሙሉ ዜግነት ትሰጣለች።

በዚህ መልኩ የማልታን ዜግነት ለማግኘት 880,000 ዩሮ የሚጠይቅ ሲሆን የቤተሰብ ቁጥር በጨመረ ቁጥር ገንዘቡም ይጨምራል።

የካሬቢያኗ ቅዱስ ኪትስና ኔቪስ ደሴቶች እንደ አውሮፓውያኑ ከ1984 ጀምሮ ዜግነት መሸጥ ጀምረዋል።

ከ2011 ጀምሮ ደግሞ ኦስትሪያ፣ቡልጋሪያ፣ሃንጋሪና ሳይፕረስም የራሳቸውን ዜግነት የመሸጥ መንገድ ቀይሰው ገበያውን ተቀላቅለዋል።

ይህ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የዋስትና ፖሊሲ እንደሆነ የሚናገሩ ባለሞያዎች አሉ።ሃብታሞች የፖለቲካ ችግርን ጨምሮ ሌሎችንም ችግሮች ማምለጥ ያስችላቸዋል።

ከዚህ ባሻገር ብዙዎች ለልጆቻቸውን የተሻለ ቢዝነስ ስለሚፈጥር የፓስፖርት ሽያጩን ይወዱታል።

ማልታ የአውሮፓ ህብረት አባልና የሸንገን ቪዛም አካል በመሆኗ በማልታ ቪዛ እንደልብ አውሮፓ ላይ መንቀሳቀስ መቻሉ የማልታን ፓስፖርት ዋጋ ከፍ አድርጎታል።

Image copyright Getty Images

የማልታ ዜግነት የማግኘት ፕሮግራም ተወዳጅ የሚሆንበት ሌላም ምክንያት አለ።ዜግነት ለማግኘት ባመለከቱ በአንድ ዓመት ወይም በአንድ ዓመት ተኩል ፓስፖርት መግኘት ይቻላል።ይህ ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር ፈጣን የሚባል ነው።

የማልታ ፓስፖርት ለማግኘት አመልካቾች 350,000 ዩሮ የሚያወጣ ንብረት እንዲገዙ አልያም በየወሩ 16,000 ዩሮ እያወጡ ለአምስት ዓመታት ለምሳሌ ቤት ሊሆን ይችላል መከራየት ይጠበቅባቸዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሰማንያ በመቶ የሚሆኑት አመልካቾች የሚመርጡት መከራየትን ነው።

የተገደሉት የማልታዋ ጋዜጠኛ ዳፍኒ ካሩዋና በአንድ ወቅት "እነዚህ ቢሊየነሮች ማልታ የመኖር ፍላጎት የላቸውም ።የሚፈልጉት ወደ አውሮፓ የሚገቡበት በር ነው።ምናልባትም ማልታ ላይ ጨርሶ እግራቸውን ላያሳርፉ ይችላሉ።ምክንያቱም ማልታ ላይ መኖር ቢፈልጉ ኖሮ ቤት ይገዙ ነበር" ብለዋል።

በሌላ በኩል ከአመልካቾች የሚገኘው ገንዘብ ቀላል የሚባል አይደለም።ይህ በአሁኑ ወቅት 220 ሚሊዮን ዩሮ የደረሰ ሲሆን ይህ ደግሞ የማልታን አጠቃላይ የገቢ ምጣኔ 2.5 በመቶ የሚሸፍን ነው።

የዜግነት ክርክር

ነገሩ ብዙ ጥቅሞች ቢኖሩትም ለብዙዎች ዜግነት ከቁጥር በላይ ነው።

"ፓስፖርት የሚሸጥ የሚለወጥ ነገር አይደለም።ፓስፖርት ያንተ ብቻ የሆነ ከደም ከዘረ- መል ጋር ግንኙት ያለው ነው"ይላሉ ከአርባ ዓመታት በላይ ማልታ ውስጥ የኖሩት ጀርመናዊት ሄልጋ ኢሉል።

እርሳቸው ከ 15 ዓመታት በፊት ነበር ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ ጀርመናዊነታቸውን ወደጎን ትተው የማልታ ዜግነታቸውን የተቀበሉት።

"ነገር ግን ዜግነት በወላጆቻችን ያገኘነው በመሆኑ በዚህ መልኩ ማግኘትን እንዴት በአዎንታዊነቱ እንመለከተዋለን?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

በቨርጂኒያ ሪችሞንድ ዩኒቨርሲቲ መምህር የፖለቲካ መምህር የሆኑት ጃቬር ሂዳልጎ ዜግነት አይሸጥ በሚለው ሃሳብ አይስማሙም።ይህ ለሳቸው አጉል መመፃደቅ ነው።

"ዜግነት ቢሸጥ ችግሩ ምንድን ነው?" በማለትም ይጠይቃሉ።

ያም ሆነ ይህ አማርና ቤተሰቦቿ ማልታ ውስጥ በገዙት ቤት በመኖር ላይ ናቸው።እሷም እህትና ወንድሞቿም እንደ እኩዮቻቸው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው።

እሷ እንደምትለው የማልታን ህይወት ተለማምደው ጎረቤትና ጓደኞችም አፍርተዋል።

ቢሆንም "ሁሉም ሰው እንደኛ እድለኛ አይደለም፤ይህ ደግሞ በጣም ያሳዝናል" ትላለች።