የየመን አማፅያን ወደ ሪያድ ያስወነጨፉት ሚሳኤል የኢራን ምርት መሆኑን የሚያሳይ ምልክት አለበት

የመን ወደ ሳዑዲ ሚሳዔል ተኮሰች

የፎቶው ባለመብት, ALMASIRAH

ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ የተወነጨፈው ሚሳኤል ከኢራን እንደተሰጠ የሚያሳይ ምልክት አለበት ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ተናገሩ።

ኒኪ ሀሊይ እንዳሉት የኢራን ድርጊት "የቀጠናውን ግጭት የበለጠ ያወሳስበዋል" ብለዋል።

ሚሳኤሉ ማክሰኞ እለት በሳዑዲ አረቢያ መከላከያ ኃይል ተመትቶ የወደቀ ሲሆን እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የተመዘገበ ጉዳት የለም።

ኢራን ሳዑዲ አረቢያን እና የየመን መንግሥትንን እየተፋለሙ የሚገኙትን የሁቲ አማፂያንን ታስታጥቃለች የሚለውን ክስ አስተባብላለች።

የሁቲ አማፅያን ቴሌቪዥን የሆነው አል ሚሲራህ እንደዘገበው 'ቡርካን ኤች2' ባሌስቲክ ሚሳኤል ኢላማ አድርጎ የነበረው በሪያድ የሚገኘውን የንጉሳውያኑን ቤተ-መንግሥት ነበር።

በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላትን ያናገሩት ሀሊይ እንዳሉት "ከዚህ ቀደም የነበሩት ጥቃቶች በሙሉ የተካሄዱት የኢራን ምልክት ባለባቸው እና ከኢራን መንግሥት በተሰጡ መሳሪያዎች ነው።"

"ሁላችንም በአንድነት የቴህራን መንግሥትን ወንጀል ማጋለጥ እና መልእክታችን ግልፅ ሆኖ እስኪገባቸው ድረስ አስፈላጊውን ሁሉ ነገር ማድረግ አለብን። ያንን የማናደርግ ከሆነ ግን ኢራን የዓለም ህዝብን ማቆሚያ ወደሌለው የቀጠናው ግጭት ውስት ጎትታ ትከታለች።"

በቴህራን መንግሥት ላይ መወሰድ አለበት ያሉትንም እርምጃ በዝርዝር ያስቀመጡ ሲሆን ከኢራን ጋር ወዳጅ የሆነችው ሩሲያ ግን ድጋፍ እንደማትሰጥ አሳውቃለች።