በቨርጂኒያ የምትኖረው አሜሪካዊት በገዛ ውሾቿ ተነክሳ መሞቷን ፖሊስ አስታወቀ

ቤትኒ ስቴፈንስ በቨርጂኒያ በገዛ ውⶄቿ ተነክሳ ሞተች

የፎቶው ባለመብት, CBS

የምስሉ መግለጫ,

ቤትኒ ስቴፈንስ እና ውሻዋ

ባለፈው ሳምንት በገጠራማዋ ቨርጂኒያ ሁለት ውሾቿን እያናፈሰች በነበረበት ወቅት ተነክሳ ስለሞተችው ሴት ፖሊስ ዝርዝር መረጃዎችን ይፋ አድርጓል።

አርብ እለት የፖሊስ መኮንኖች ውሾቹን ሲያገኟቸው መጀመሪያ ላይ የሞተ እንስሳ አጠገብ የቆሙ መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን አስክሬኑ የ ስቴፈንስ ሲሆን ውሾቹም እየበሏት ነበር።

ማስጠንቀቂያ፤ ከዚህ በታች ያለው ዝርዝር አንዳንድ ሰዎችን ሊያበሳጭ ይችላል

"እኔ እና አራት መኮንኖች ያየነው ውሾቹ የሴትየዋን አካል እየዘነጣጠሉ ሲበሏት ነው።" ብለዋል የጉችላንድ አውራጃ ፖሊስ አዛዥ ጂም አግኒው።

"የመጀመሪያው አስደንጋጭ ጥቃት የደረሰባት አንገቷና ፊቷ ላይ ነው"

"ከዛም መሬት ላይ ወደቀች፣ ራሷንም ስትስት ነፍሷ እስኪወጣ ድረስ ቦጫጨቋት" በማለት በርካታ ጊዜ እረፍት እየወሰዱ አስረድተዋል።

የፖሊስ አዛዡ አግኒው ይህንን ዝርዝር መረጃ ለቤተሰቧ ደህንነት ሲባል መጀመሪያ ላይ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ማድረግ አልፈለጉም ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Kristin Smith

የምስሉ መግለጫ,

ቤትኒ ቶንካ እና ፓክማን ከሚባሉ ውሾቿ ጋር

ጓደኞቿ ግን እነዚህን ውሾች ከቡችልነት ጊዜያቸው ጀምራ ያሳደገቻቸው ነች ታዲያ እንዴት ሊገሏት ቻሉ ሲሉ ይጠይቃሉ።

አንድ ባርባራ ኖሪስ የተባለች ጓደኛዋ ውሾቹ በጣም ጥሩዎች ናቸው ''እየላሱ ካልገደሏት በቀር" ብላለች ለ ደብሊው ደብሊው ቢቲ ኒውስ።

ፖሊስ የቤተሰብ ፍቃድን ካገኘ በኋላ ውሾቹን ገድሏል። ሁለቱ ውሾች ከስቴፈንስ ሁለት እጥፍ ይመዝናሉ።

ውሾቹ ቶንካ እና ፓክማን የሚባሉ ሲሆን አርብ እለት ስቴፈንስ ከጠፋች በኋላ አባቷ ፍለጋ ወጥቶ በጫካው ውስጥ አግኝቷቸዋል።

"ስቴፈንስ ክፉኛ ተጎድታ ነበር፤ ስናገኛት ከሞተች ቆይታ እንደነበር ማወቅ ችለናል" ብለዋል አዛዥ አግኒው ለጋዜጠኞች፤ በደም የተነከረ ልብሷ አስክሬኗ አካባቢ ተበታትኖ እንደነበረም አክለዋል።

"ያልተነከሰ የአካል ክፍል አልነበራትም" በማለት ስለሁኔታው አብራርተዋል።

ባለስልጣናት በጭንቅላቷ ላይ ያለው ንክሻ የውሾቹ መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን ለተጨማሪ ምርመራም የውሾቹ አካል ተቀምጧል።