ደዳብ፡ በዓለም በትልቅነቱ ሁለተኛ የሆነው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ፈተና ውስጥ ወድቋል

የደዳብ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ኬንያ Image copyright TONY KARUMBA
አጭር የምስል መግለጫ የደዳብ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ

አቶ ኢድሪስ መሐመድ ይባላሉ። ወደ ደዳብ የስደተኞች መጠለያ የመጡት እኤአ በ2007 መሆኑን ይናገራሉ።

በመጀመሪያ ገና የ15 ዓመት ወጣት እያሉ ወደ ሶማሊያ መሰደዳቸውን የሚናገሩት አቶ ኢድሪስ በኬንያ በሚገኘው በዚሁ የመጠለያ ጣቢያ ከ 10 ዓመታት በላይ መቆየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት በተወለዱበት ባሌ አጋርፋ ከተማ አባታቸው ፊት ለፊታቸው ሲገደሉ እሳቸው እና እናታቸው እግራቸው ወደመራቸው አቅጣጫ አቀኑ፤ ይህ ከኢትዮጵያ ለመውጣት ዋነኛ ምክንያት ሆናቸው።

ከዚያም ካገኙት ሰው ጋር ሶማሊያ በመግባት ኑሯቸውን መሰረቱ። ባጋጠማቸው ችግር ከስድስት ልጆቻቸው እና ከሶማሊያዊት ሚስታቸው ጋር ወደ ደዳብ የስደተኞች መጠለያ መጥተው መኖር ጀመሩ።

"ሕይወት በመጠለያ ጣቢያው በጣም ከባድ ነው። ይሁን እንጂ ሀገራችን ውስጥ የሚሰማው ወሬ እንድንመለስ የሚጋብዝ ሆኖ አላገኘነውም። ከሰውም ሆነ ከሚዲያ በምንሰማው ነገር ውስጣችን ያዝናል" በማለት ተናግረዋል።

አቶ ኢድሪስ ልጆቻቸው የተወለዱት በባዕድ ሀገር በመሆኑ ሀገራቸውን፣ ባህላቸውን እና ቋንቋቸውን ለማወቅ አልታደሉም።

ልጆቹ ሁልጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እንዲወስዷቸው ቢጎተጉቷቸውም ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ በመፍራት ጥያቄያቸውን ለመመለስ አለመቻላቸውን ይናገራሉ።

የአቶ ኢድሪስ ስጋት ወደ ሀገር መመለስ አለማቻል ብቻ ሳይሆን ተጠልለው የሚገኙበት እና ቀንን እገፋበታለሁ ያሉት ደዳብ የስደተኞች መጠለያ የመዘጋት ወሬ ጭምር ነው።

"ይህ ሥፍራ ሕይወታችንን ለማዳን የተሸሸግንበት ነው፤ ይዘጋል ሲባል ትልቅ ሐዘን ነው የተሰማን፤ የምንለው ነገር የለም፤ ግራ የገባው ሰው ነን " በማለት የተሰማቸውን ስጋት ገልፀዋል።

አጭር የምስል መግለጫ አቶ ኢድሪስ መሐመድ በደዳብ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ

አቶ አለማየሁ ወርዶፋም ከ2006 ጀምሮ በመጠለያው መኖር መጀመራቸውን ይናገራሉ። በአጠቃላይ ላለፉት 25 ዓመታት በየመን፣ ሶማሊያ እና ሱዳን በስደት መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ አለማየሁ በፖለቲካ ምክንያት በደረሰባቸው ጫና እና ወከባ ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ከሀገር መውጣታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሽምግልና ዕድሜያቸው በስደት ሀገር የሚኖሩት አቶ አለማየሁ ልጆቻቸውም በተለያየ ሀገር ተበትነው እንደሚገኙ ይገልፃሉ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
"ቤተሰቦቼን ጥዬ በስደት ዕድሜዬን እየጨረስኩ ነው"

"የዚህ መጠለያ ኑሮ ከባድ ነው። ወደ ሶስተኛ ሀገር የመሄድ እድል እንኳ ከሌሎች እኩል አይሰጠንም። ለምሳሌ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ከኛ መካከል አንድም ሰው የመሄድ እድል አላገኘም። መጠለያ ለማግኘት ራሱ በእኩል አይን አንታይም፤ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ከሌሎች ሀገር የተለየ ነው በሚል ሰበብ ነፃ የትምህርት እድል እንኳ ተነፍገናል"በማለት በመጠለየዓው የሚደርስባቸውን ችግር ዘርዝረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አለም አቀፉ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃለመጠይቅን ያላለፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከአስር ዓመት በላይ በድርጅቱ ሳይመዘገቡ አልያም ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ የሚበሉት እስከማጣት ድረስ ተቸግረው በመጠለያው ኑሯቸውን በመግፋት ላይ እንዳሉ ተናግረዋል።

የደህንነት ጉዳይ ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት አቶ አለማየሁ በቅርቡ አራት ኢትዮጵያውያን በጩቤ ተወግተው ህይወታቸው ማለፉን ያስረዳሉ።

ፖሊሶች በርቀት ስለሚገኙ በመሳሪያ አስፈራርተው ንብረታቸውን እንደሚዘረፉ ተናግረዋል።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በቅርቡ የደዳብ ስደተኞች መጠለያ መዘጋትን ወሬ ሲሰሙ ቀኑ ጨልሞባቸዋል።

በዚህ መጠለያ ጣቢያ ከሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን መካከል ደግሞ ካርሎስ ተስፋዬ ሌላኛው ነው።

"ስመጣ ብቻዬን ብሆንም አሁን ግን ትዳር መስርቼ አራት ልጆችን አፍርቻለሁ" ይላል ካርሎስ።

ካርሎስ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲላ አካባቢ ይኖር የነበረ ሲሆን በሱና በቤተሰቡ ላይ በደረሰው ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ሀገር ለቆ ለመውጣት መገደዱን ይናገራል።

አጭር የምስል መግለጫ አቶ ካርሎስ ተስፋዬ በደዳብ ስደተኞች መጠለያ ጣብያ

ወደዚህ መጠለያ ጣቢያ ስመጣ የደህንነት ስጋቱ ከፍተኛ ነበር። የመሣሪያ ተኩስ በየጊዜው ይሰማ ነበር የሚለው ካርሎስ ሁለት ጊዜ ዝርፊያ እንዳገጠመው ተናግሯል።

"ሃያ ዓመት በስደተኝነት በርካታ ነገሮችን አልፌ ብኖርም አሁን ግን መቋቋም የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ። ልጆቼን ትምህርት ቤት መላክ አልቻልኩም። ስለዚህ በዚህ ሁኔታ እዚህ ለመኖር በጣም ከብዶኛል።"

በልጆቼ ምክንያት ወደ ሀገሬ መመለስ አልችልም የሚለው ካርሎስ "ወደ እዚህ ከመጣ ጀምሮ ይዘጋል የሚል ወሬ ሁሌ ስለምሰማ ፈጣሪዬን ብቻ ተስፋ አድርጌ ነው የምኖረው" ሲል ይናገራል።

የደዳብ የስደተኞች መጠለያ የወደፊት እጣፈንታ

አጭር የምስል መግለጫ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ

የስደተኞቹን አኗኗር ለመጎብኘት ወደ መጠለያው ያቀኑት የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ የመጠለያው የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማስኬድ የበጀት እጥረት እንዳጋጠመ ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም ድጋፍ ያደርጉ የነበሩ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታቸውን ማቋረጠቸውን ተከትሎ የበጀት እጥረቱ እንደተፈጠረ አስታውቀዋል።

ኮሚሽነሩ በደዳብ ያለውን ችግር ለመፍታት ኮሚሽኑ ከኬንያ እና ከሶማሊያ መንግስታት ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

"እስካሁን 32 ሺ የሶማሊያ ስደተኞች ወደ ኪስማዮ ተመልሰዋል። በቅርቡም ደግሞ 20 ቤተሰቦች ወደ አገራቸው ይመለሳሉ" ይላሉ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ።

የኬኒያ መንግስት መጠለያ ጣብያው እንዲቀጥል ፍላጎት ባይኖረዉም አሁን ግን መግባባት ላይ ደርሰናል ያሉት ግራንዲ የመጠሊያውን ችግር ለመፍታት የዓለም ባንክ እና ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶችን ተማፅነዋል።

ስደተኞቹንም "ታጋሽ ሆኜ አብረን እስከሰራን ድረስ አይዘጋም፤ አትስጉ። እዚሁ መቀጠላችን ጥያቄ የለውም" ሲሉ አፅናንተዋል።

በደዳብ መጠለያ ጣብያ የሚገኙ ስደተኞች ከሚሰጣቸው የምግብ እርዳታ በተጨማሪ ኣቅማቸዉ ያሳድጉ ዘንድ የተለያየ ስልጠና እየተሰጣቸዉ ይገኛል።

በመጠለያ ጣብያው ሴቶችና ህጻናት በብዛት የሚገኙ ሲሆን ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዉ የተሰደዱ ሴቶች በመጠለያው የምክር ኣገልግሎት ያገኛሉ።

ለ26 አመታት አገልግሎት የሰጠው ደዳብ በአሁኑ ሰአት ከ200 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን ጨምሮ የሌሎች አገራት ስደተኞችን ይገኙበታል።