''አዲስ ነገር ያልታየበት'' የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ

ኢህአዴግ

በኢህአዴግ አባላት ፓርቲዎች መካከል ውጥረት መኖሩን የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። ውጥረቱ ደግሞ በህዝቦች መካከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና ግጭቶች ወቅት ይበልጥ ሰፍቶ ታይቷል። በዚህ ወቅት ነው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዝግ ስብሰባ የገባው። የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ገልፀው ነበር።

የሥራ አስፈፃሚው ስብሰባው ታህሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም የጀመረ ቢሆንም ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አልታወቀም። በትናንትናው እለት የስብሰባውን አለመጠናቀቅ የሚያመለክት መግለጫ ከኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ወጥቷል።

መግለጫው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ዓመት የተጀመረውን 'በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ' አፈፃፀም በዝርዝር መገምገም መጀመሩን አስቀምጧል፡፡ በመቀጠልም ከነባራዊው ሁኔታ ጋር የሚመጥን ድርጅታዊ ቁመና ለመያዝ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግም ቃል ገብቷል።

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እስካሁን ባደረገው ግምገማ በአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት በተለይም ''ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የርስ በርስ መጠራጠር ያመዘነበት፣ አለመተማመን ቀስ በቀስ እየገነነ የመጣበት መሆኑን'' መገንዘቡንም አስቀምጧል።

''በአሁኑ ወቅት የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅታችን አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው'' በማለት በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ላለችበት አስጊ ሁኔታ የአመራሩ ድክመት ያደረገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብሏል።

በመጨረሻም የሕዝቦችን ጥያቄ በተሟላ መልኩ ለመመለስና ለፌዴራል ሥርዓቱ በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥም ቃል ገብቷል።

አዲስ ነገር የለም

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክና የሥነ-ጥበብ ታሪክ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ አበባው አያሌው ለይሰሙላ የወጣ መግለጫ ነው ይላሉ።

ምክንያታቸውንም ሲያስቀምጡ በህዝቡ መካከል እርስ በእርስ አልተስማሙም የሚል ወሬ በዝቶ ነበር። ይህንን ወሬ ለማክሸፍ ወይንም አለን ጥሩ ሁኔታ ላይ ነን፤ ለማለት የወጣ መግለጫ ነው እንጂ ችግሮችን እና የስብሰባውን ሂደት በዝርዝር የሚያሳውቅ አይደለም ብለዋል።

ከፍተኛ አመራሩ ሥራ አልሰራም ሲሉ የገለፁት አቶ አበባው፤ ይህንን ደግሞ ማንኛውም ተራ ህዝብ የሚያውቀው ነገር ነው ብለዋል። ከዚያ ይልቅ ሊመጡ የሚችሉ ለውጦችን ቢነግሩን መግለጫው ትርጉም ያገኝ ነበር ሲሉም ያክላሉ።

የኢዴፓ የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። መግለጫው ያነሳው ነጥብ ለኢህአዴግ ይሆናል እንጂ ለህዝቡ አዲስ አይደሉም፤ ሕዝቡ ከ 10 ዓመታት ወዲህ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እያነሳ ይናገር የነበረው እና ኢህአዴግ አልቀበል ያለው ነጥብ ነበር ብለዋል።

ሀገሪቷ የምትታመስበት የብሄር ግጭት በሕዝቦች፣ በክልል በሚገኙ የፖሊስ አባላትና በትምህርት ተቋማት ደረጃ እየተካሄደ እያለ በዚህ ላይ ውይይት አካሂደው ከሆነ ለምን አይገልፁልንም? ሲሉ ይጠይቃሉ አቶ አበባው።

አቶ ሙሼ በበኩላቸው ታህሳስ 3 የተጀመረ ስብሰባ የእርስ በእርስ ንትርክ መኖሩና መግባባት ላይ መደረሱን እንጂ በአጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ሀገሪቱ አሁን በደረሰችበት ደረጃ ላይ እንኳን አቋም መውሰድ አልቻሉም ብለዋል።

የኢህአዴግ የአሁኑ መግለጫ ከዚህ ቀደም በህወሓት ስብሰባ ወቅት የተነሱ እና የተነገሩ ነጥቦች ናቸው። ይኸው ሃሳብ በጎንደሩ ስብሰባ ላይም ተነስቷል። በባህር ዳሩም የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ወቅትም ተነስቷል። ስለዚህ መግለጫው ምንም አዲስ ነገር አይናገርም ሲሉ ይጨምራሉ አቶ አበባው።

የመድረክ ሥራ አስፈፃሚና የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹም መግለጫው ግልፅ አይደለም ብለዋል፤ ከዚህ በፊት እንደተለመደው ሕዝቡን ለማማለል ለተከሰቱ ችግሮች አመራሩን ተጠያቂ እንደሆነ ቢያስቀምጥም የተለየ ነገር አልተጠቀሰም ሲሉም ሃሳባቸውን ያብራራሉ።

ከዚያ ይልቅ ግን ፓርቲው ወደፊት ሊወስድ የሚያስባቸውን የኃይል እርምጃዎች የሚያመለክቱ ነገሮች አሉበት። ምናልባትም የሲቪል አስተዳደሩን ወደ ወታደራዊ ለመቀየር ዕቅድ ያለው ይመስላል ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

መጠራጠር

መጠራጠር የሚለው ነገር ለኔ አልገባኝም የሚሉት አቶ አበባው ከዛ ይልቅ ሁለቱ ፓርቲዎች፤ ብአዴን እና ኦህዴድ ባለው መንገድ አንቀጥልም የአንድ ፓርቲ የበላይነት መቅረት አለበት እንደሚሉ ነው የሚገባኝ ብለዋል።

ምክንያታቸውንም ሲያብራሩም እስካሁን በነበረው የኢህአዴግ ጉዞ በአራቱ ፓርቲዎች መካከል የጎንዮሽ ግንኙነት የለም። አሁን ግን ወደ የአቻ ለአቻ ግንኙነት እንምጣ የሚል ነጥብ እንደተነሳ አውቃለሁ ብለዋል። መጠራጠር ሳይሆን የአቻነት ጥያቄ ነው ያለው ይላሉ አቶ አበባው።

አቶ ሙላቱ ደግሞ አንድ ሥርዓት በሥልጣን ላይ ብዙ በቆየ ቁጥር መጠራጠርና መሰለቻቸት እንደሚመጣ፤ ታዛዥነትና መከባበርም እየጠፋ እንደሚሄድ ይገልፃሉ።

የፓርቲው አባላት ከሕዝቡ የወጡ እንደመሆናቸው የሕዝብን ጥያቄ መጋራታቸው አይቀርም። ይህ ደግሞ ቀስበቀስ እየተጠናከረ በመሄድ ችግር ወደመፍጠር ይሄዳል። ይህንን ደግሞ መገንዘብ ነበረባቸው፤ ስላልተገነዘቡት አሁን የደረሱበት እርስበርስ መጠራጠር ላይ ደርሰዋል ሲሉ ያብራራሉ።

አቶ ሙሼ የእርስ በእርሱን መጠራጠር ያመጣው ድርጅቱ ከላይ እስከታች የሕዝብ ፍላጎትን ከማስከበር ይልቅ የድርጅት ፍላጎትን በማስጠበቅ የተጠመደ በመሆኑ የተጠቀመ እና ያልተጠቀመ ድርጅት ግጭት ማስከተሉ አይቀርም ብለዋል።

ይህ ደግሞ ለረዥም ጊዜ አስተያየት ሲሰጥበትና ሲተችበት የነበረው ሁኔታ ነው ሲሉ መጠራጠር የሚለውን ሃሳብ አሮጌነት ይተቻሉ።

ምን ይጠበቃል

ያለነው ገደል ጫፍ ላይ ነው የሚሉት አቶ አበባው የሀገሪቱን ሁኔታ አሁን የመን እና ሶሪያ ወዳሉበት እየሄደ ነው ሲሉ ይሰጋሉ።

ይህን ያመጣው ደግሞ ፖለቲካው ብሄረተኝነትን ስላከረረውና የፖለቲካውም፣ የማህበራዊው ሕይወቱም፣ የተቋማትም ግንኙነት ማጠንጠኛ ስላደረገው ነው።

ስለዚህ የብሄር ፖለቲካን ለውጥ የሚያደርጉበት እንዲሁም በፖለቲካ እና በኢኮኖሚው የአንድን ወገን የበላይነትን አስቀራለሁ የሚል ለውጥ እጠብቃለሁ ብለዋል።

አቶ ሙላቱ ሁሉንም ወደሚጠቅም ወደ መልካም ነገር ይመጣሉ የሚል እምነት የለኝም ይላሉ። "በቻሉት መጠን ሥርዓቱን ለማስቀጠል ጥረት የሚያደርጉ ይመስለኛል።"

ይህ ደግሞ ያለውን ችግርና ብሶት የሚያባብስና የሃገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው የሚሆነው ብለዋል። በዚህ ደግሞ እየታዩ ያሉት ግጭቶች እየተካረሩ ይመጡና የሃገር አንድነትና የሕዝብን ደህንነትን እስከማናጋት ሊደርስ ይችላል ሲሉ የአቶ አባባውን ሃሳብ ይጋራሉ።

የፓርቲውን ህልውና ለማስቀጠልና ሀገሪቱንም ከከፋ ችግር ማዳን የሚፈልጉ ከሆነ ከሁሉም ወገኖች ጋር በመነጋገር ለችግሮች መፍትሄ ለማምጣት መሥራት አለባቸው ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

አቶ ሙሼም በበኩላቸው የኢህአዴግ ስብሰባ በጣም ሚስጥራዊ ከመሆኑ የተነሳ ይህ ይሆናል አይሆንም ብሎ መገመት ከባድ ነው። ነገር ግን ለብሔር ግጭቶች መፍትሄ ይዞ ይወጣል ብዬ ግን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

በማስከተልም ፓርቲዎቹ በዚህ ስብሰባ መግባባት ላይ ባይደርሱ በሽኩቻው አሸናፊ የሆነው ቡድን የተጠናከረ ሃይል ይዞ አገሪቷን የሚመራበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

ሌላኛው ደግሞ ፓርቲዎቹ ሽኩቻቸውንና መለያየታቸውን ወደ ህዝብ ይዘዉት ከወረዱ አለመረጋጋት እና ብጥብጥ ሊያስከትል ይችላል።

ሦስተኛው የአገሪቱን ደህንነትና ጸጥታ ማስከበር ያለበት አካል አገሪቷ አደጋ ላይ ነች ብሎ ካመነ እድሉን ተጠቅሞ በጊዜያዊ አዋጅ አማካኝነት እመራለሁ ብሎ ስልጣን ሊይዝ ይችላል ብለዋል።

አቶ ሙሼ ሃሳባቸውን ሲያጠናቅቁም ከመንግሥት የህግ የበላይነት ማስፈን፣ የዜጎችን ደህንነትና ፀጥታ መጠበቅና ማስከበር ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

"ሥርዓቱ ይሆናል እንጂ አገር አትበታተንም"

ተያያዥ ርዕሶች