የኡጋንዳ ሕዝብ እንደራሴዎች የፕሬዝዳንቱን የእድሜ ገደብ አነሱ

ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪ ኡጋንዳን ከ 30 ዓመታት በላይ መርተዋል

የኡጋንዳ ሕዝብ እንደራሴዎች አሁን ያሉት ፕሬዝዳንት ለስድስተኛ ጊዜ በስልጣን እንዲቆዩ የሚያስችላቸውን ሕገ-መንግሥታዊ ለውጥ አፀደቀ።

ሦስት ቀን ከፈጀ ክርክር በኋላ የፕሬዝዳንቱን የእድሜ ጣሪያ የሚገድበውን የሕገ-መንግሥት አንቀፅ እንዲሻሻል በከፍተኛ ድምፅ አፅድቀዋል።

ይህም ማለት ኡጋንዳን ከ30 ዓመታት በላይ የመሩት የ73 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በ2021 ለዳግም ምርጫ መወዳደር ይችላሉ።

በ2005 ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደር እንዲችሉ የሚያደርገውን የስልጣን ጊዜ ገደብ አንስተው ነበር።

ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ የሕይወት ዘመን መሪ ይሆናሉ የሚለውን ትችት ተከትሎ አንቀፁ ወደነበረበት ተመልሷል።

የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች እንደመከራከሪያ ያቀረቡት ኡጋንዳውያን በፈለጉ ሰዓት ከስልጣን ሊያወርዷቸው ይችላሉ የሚል ነው።

ተቃዋሚ የሕዝብ እንደራሴዎች ከአንድ ጊዜ በላይ ክርክሩን አቋርጠው የወጡ ሲሆን ስድስት አባላት በህጉ ላይ ተቃውሞ በማድረጋቸው ታግደዋል።

የሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያው በፕሬዝዳንቱ ፓርቲ ለህዝብ እንደራሴዎቹ መስከረም ላይ የቀረበ ሲሆን ፓርላማው በዚህ የተነሳ ተረብሾ ነበር።

በወቅቱ ከህዝብ እንደራሴዎቹ መካከላል ሽጉጥ የያዘ ሰው እንዳለ በተሰማ ጭምጭምታ በፓርላማ አባላቱ መካከል ግብግብ ተፈጥሮ ነበር።

የፓርላማው አፈ-ጉባዔም ሽጉጥ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ፍተሻ እንዲካሄድ ያዘዙ ሲሆን የኡጋንዳ መገናኛ ብዙሃን ለማጣራት እና ለማረጋጋት 20 ደቂቃ መውሰዱን ዘግበዋል።

የፕሬዝደንትነት ዕድሜ በኡጋንዳ አጨቃጫቂ የሆነበት ምክንያት የሀገሪቱ ርዕሰ-ብሄር ዩዌሪ ሙሴቬኒ አሁን ላይ ዕድሜያቸው 73 ሲሆን የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ግን አንድ ፕሬዝደንት ከ75 ዓመት በላይ እንዲያገልግል አይፈቅድም።

ዋነኛ ተቃዋሚ የሆኑ ግለሰብ በማሻሻያው ላይ ተቃውሞ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች