ካለሁበት 15፡ "ራሴንና ልጆቼን የሰሜን ተራሮች ላይ ባገኝ በጣም ደስ ይለኝ ነበር"

ፌቨን ተወልደ Image copyright FEVEN TEWELDE

ፌቨን ተወልደ እባላለሁ፤ የምኖረው በፈረንሳይ ፓሪስ ነው ።

እዚህ ከመምጣቴ በፊት በአዲስ አበባ ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት በአውሮፓውያኑ 2002 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንደጨርስኩኝ በሊዮን ከተማ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ዕድል አግኝቼ ነበር።

እዚያው የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከጨረስኩኝ በኋላ ደግሞ ለአንድ ዓመት በዩናይትድ ኪንግደም በርሚንግሃም በትምህርት ልውውጥ መርሃግብር አሳለፍኩኝ።

ከዚያ ስመለስ ግን ባለቤቴ ፓሪስ ሥራ ስላገኘ የመጨረሻውን ዓመት በፓሪስ ነው የተማርኩት።

አሁን እኔም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የባህልና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) ኢትዮጵያ በምትወክልበት ክፍል ውስጥ እሠራለሁ።

የፓሪስን ሥነ-ሕንፃ ጥበብ፣ እንደ አይፍል ማማ ያሉ ልዩ መስህቦቿን፣ አስገራሚ ታሪካዊ መገለጫዎችና ልዩ የመታሰቢያ ሃውልቶቿን ሳይ ታሪኳንና ባህሏን የምትገልጽበት መንገድ በጣም ለየት እንደሚያደርጋት አስባለሁ።

ከምግቦቿ ደግሞ ታርቲፍሌት የሚባለውን ከድንች ቺዝና ከሥጋ የሚሠራ ምግብ በጣም ደስ እያለኝ ነው የምበላው።

በተለይ በብርድ ጊዜ በደንብ ስለሚያሞቅ፣ ሆድም በደንብ ስለሚሞላ በደንብ ነው የምመገበው።

Image copyright FEVEN TEWELDE
አጭር የምስል መግለጫ ከፈረንሳይ ምግቦች 'ታርቲፍሌት' የተሰኘውን ምግብ ነው

ከኢትዮጵያ ከምንም በላይ የሚናፍቀኝ ተሰብስቦ ቡና መጠጣቱ ሳይቻኮሉ ጊዜ ወስዶ ከሰው ጋር መወያየቱ ነው፤ እዚህ ለሁሉም ነገር ጊዜ ያጥራል።

በፓሪስ ቤቴ ቁጭ ብዬ በማዕድ ቤቴ መስኮቴ በኩል የሚታየኝ አነስ ያለ ግን ዓይን የሚሞላ አረንጓዴ ቦታ ሲሆን ደስ የሚለኝ ውብ ዕይታዬ ነው።

ምክንያቱም እዚህ ሀገር ሁሉም ዕይታ ከወቅቱ ጋር ሰለሚቀያየር ለውጦቹን በደንብ የሚነግረኝም፣ የሚያስታውሰኝም ይህ ቦታ ነው።

Image copyright FEVEN TEWELDE
አጭር የምስል መግለጫ የሁለት ወቅቶች ዕይታ

በፓሪስ በጣም ያስገረመኝና በሀገሬ ከለመድኩት ታላላቆቻችንን የማክበር ልምድ ጋር የሚቃረነብኝ ነገር በባቡርም ሆነ በአውቶብስ ስሄድ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን አይቼ በመነሳት ይመርቁኛል ብዬ ስጠብቅ እነርሱ ግን ትልቅ ናቸው ብዬ ማሰቤ ሲያናድዳቸው አያቸዋለሁ።

የመቻል አቅማቸውን የተጠራጠርኩ አድረገው ሲወስዱ በተደጋጋሚ ስለገጠመኝ ከዚያ በኋላ ብዙ አስቤ፣ ተጠንቅቄ ነው የምነሳው።

አንድ ቀን ግን በእግሬ ወደ ቤቴ ስመለስ አንዲት በዕድሜ የገፉ ምናልባትም ወደ 90 የተቃረቡ እናት መራመድ አቅቷቸው ድክም ብለው ሳይ አላስችል አለኝና ፈራ ተባ እያልኩ ተጠጋሁ።

በአጋጣሚ ግን እውነትም እርዳታ የሚፈልጉ ነበሩና ደስ ብሏቸው 'እባክሽን ቤቴ ድረስ ደግፈሽኝ እንሂድ፤ እያዞረ እየጣለኝ ነው' ሲሉኝ ሀገሬ እያለሁ ይህን በማድረጌ ብቻ ይዘንብልኝ የነበረውን ምርቃት አስብኩኝ ።

ሌላው የታዘብኩት እኛና ፈረንሳውያንን የሚያመሳስለን ነገር ለባህላችን የምንሰጠው ቦታ ነው።

እዚህም ልክ እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በባህሉ በጣም የሚኮራና ከየትኛውም ሀገር የተለየ እንደሆነ የሚያስብ ሕዝብ ነው ያለው።

ይህ አቋማቸው በሥልጣኔ አለመደብዘዙ ይገርመኛል።

Image copyright FEVEN TEWELDE
አጭር የምስል መግለጫ ፌቨን ከባለቤቷ እና ከልጆቿ ጋር

ሌላው ሁሌም ኢትዮጵያን የሚያስታውሱኝ ፓሪስ የሚገኙት 14 የሚሆኑት የሀገር ቤት ባህላዊ ምግብ ቤቶች ናቸው ።

በሙዚየም ውስጥ ስለኢትዮጵያ ታሪክና ባህል የሚዘከርበት ቦታ ብዙ ነው።

በእስካሁኑ ቆይታዬ ያዘንኩበት ነገር ልክ ትምህርቴን እንደጨረስኩኝ የትምህርትና የሥራ ልምዴን ሳደራጅ (ሲቪ ሳዘጋጅ) በወቅቱ የነፃ አገልግሎት የምሰጥበት ክፍል ኃላፊ ዕድሜዬን አይቶ 'የትዳር ሁኔታ የሚለውን ያላገባ በይው' አለኝ።

ያኔ 26 ዓመቴ ነበር እና 'ለምን?' ስለው ከዚ በኋላ አግብታለች፣ ቀጣዩ ነገር ደግሞ መውለድ ነው ብለው ስለሚያስቡ ሥራ ማግኘት ከባድ ይሆንብሻል አለኝ።

በሰለጠነችው አውሮፓ ይህን ስሰማ የሴት እኩልነት ጉዳይ እንዲህ ባፈጠጠ መልኩ እንዳለ መቀበል ከብዶኝ ነበር።

ከዚህ ውጩ በፓሪስ ከተማ ውስጥ አንዳች ነገር የመቀየር አቅሙ ቢኖረኝ ኖሮ ከጋራ መኖሪያ ቤት ይልቅ መሬት ላይ ግቢ ያለው ቤት ቢኖረኝ ብዬ እመኛለሁ፤ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ኑሮ ማለት ነው።

ይህን ለማድረግ ደግሞ ከሥራ ቦታዬ ራቅ ማለት ስላለብኝ ቤት እስክደርስ ብዙ ጊዜ ይፈጅብኛል።

ነገር ግን ሁለት ልጆች ስላሉኝ ሩቅ ከሄድኩ ልጅ የሚይዝልኝ ያስፈልገኛል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከልጆቼ ጋር ማሳለፍ የምችለውን ጊዜ ይገድብብኛል፤ ስለዚህ ሁለቱን ማስታረቅ ስለማልችል ለልጆቼ አደላለሁ።

ሆኖልኝ ራሴን በቅጽበት ወደ ኢትዮጵያ መውሰድ ብችል እራሴንና ልጆቼን የሰሜን ተራሮች ላይ ባገኝ በጣም ደስ ይለኝ ነበር።

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገረቻት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦

ካለሁበት 16 ፡ 'ጭራሹኑ መጥፎ ነገሮች እንዳይከሰቱ ማድረግ ብችል ደስታዬ ወደር የለውም'

ካለሁበት 17 ፡ ከሰው አልፎ ለእንሰሳት ቦታ በሚሰጥበት ከተማ ውስጥ ነው የምኖረው

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ