የአዲስ አበባው ውይይት- የደቡብ ሱዳን ዜጎች እንግልት ማብቂያ ?

አቶ መለስ ዓለም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ
አጭር የምስል መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም

የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች ጦርነትን ለማቆም፣ የዜጎችን ደህንነትን ለመጠበቅና እና ለተጎዱት ሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ እንዲያስችል ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ እየተስማሙ እንደሚገኙ ሪፖርተራችን ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው የሃገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በ2015 የተፈረመውን የሰላም ሥምምነት ለመተግበር በጥሩ ሁኔታ እየተወያዩ ነው።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም የአሁኑን የውይይት መድረክ እየመሩ የሚገኙት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ኢጋድ አባል ሃገራት ሚኒስትሮች ናቸው።

የፖለቲካ ኃይሎች፣ ማህበራዊ ተቋማት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ሃሳባቸው በዚህ ውይይት ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል ብለዋል።

ይህም በሃገሪቱ ሰላምን በማረጋገጥ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለማስቆም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መደረሱን ያሳያል ብለዋል።

በ2013 ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ምክትላቸውን ዶ/ር ሪክ ማቻርን ከሥልጣን ካባረሩ በኋላ ወደ ጦርነት የገባችው ሀገር ከፍተኛ በሆነ አጣብቂኝ ውስጥ ትገኛለች።

ታጣቂዎች የተለያየ ቡድን በመፍጠር እርስ በርስ ብሎም በስልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር እየተዋጉ ይገኛሉ።

በዚሁ ጦርነትም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል እንዲሁም የአገሪቱ ኢኮኖሚም አሽቆልቁሏል።

በአሁኑ ሰዓት በደቡብ ሱዳን ከ1 ሺህ % በላይ የዋጋ ግሽበት ታይቷል። የመንግስት ሰራተኞችም ደመወዝ ከተከፈላቸው ዓመት አልፏቸዋል።

ከሀገሪቱ ዜጎች መካከል 1/3ኛው ከቀያቸው ሲፈናቀሉ ከ 2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለስደት እንደተዳረጉ አቶ መለስ ገልፀዋል።

በዚህ ውይይት መግባባት ላይ ካልተደረሰ ግን የተባበሩት መንግሥታት፣አውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት በሀገሪቱ ላይ አስገዳጅ እርምጃ ለመውሰድ ቆርጠዋል ብለዋል።

የፖለቲካ ኃይሎች እያደረጉት የሚገኘው ምክክር በስምምነት ከተጠናቀቀ በመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ተኩስ ፈፅሞ በማቆምና በመንግሥት መዋቅር እንዲሁም በሽግግር ጊዜ ደህንነት ሁኔታ ላይ ምክክሮች እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።