ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?

ከሶማሊያ የተፈናቀሉ ስደተኞች በሐማሬሳ የመጠለያ ጣቢያ
አጭር የምስል መግለጫ ሐማሬሳ የመጠለያ ጣቢያ

በኦሮሚያ እና ሶማሌ ድንበር ግጭት ምክንያት ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለዋል። ከ 4 ወር በላይ በሐማሬሳ መጠለያ የኖሩት አቶ አህመድ መጠለያው ከላሜራ ብረት ስለተሰራ ለሊት ቅዝቃዜው ቀን ደግሞ ሙቀቱ ለተለያዩ ችግሮች እንደዳረጋቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተለይ እናቶችና ህፃናት ለተለያዩ የጤና እክሎች እንደተዳረጉ ገልፀው እየተደረገ ያለው ድጋፍ ግን ጥሩ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሰፈራ

የተፈናቃዮች ድጋፍ አስተባባሪና መልሶ ማቋቋም ኮሚቴ ተፈናቃዮቹን ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ ከተሞችና በክልሉ በሚገኙ ዞኖች ውስጥ ለማስፈር ዝግጅት እያጠናቀኩ ነው ብሏል።

የኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር አበራ ደሬሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተፈናቃዮቹ የኋላ ታሪክ እና የወደፊት ፍላጎታቸው ተጠንቶ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

በንግድና ከተሞች አካባቢ የሚሰሩ ስራዎችን ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳደሩ ሰዎችን በፊንፊኔ ዙሪያ በሚገኙ ልዩ ዞኖች ለማስፈር ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ብለዋል።

"መሬት ተለይቶ የቤት ዲዛይን ወጥቶ የቤቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው። እዚያ ምን ሰርተው ይኖራሉ የሚለውን ጉዳይ ደግሞ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ጥናት እያደረጉ ነው። ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ስለ ሚኖራቸው ማህበራዊ ግንኙነትም እንደዚሁ እየተጠና ነው"።

ለመጀመሪያውም ዙር በነዚህ አካባቢዎች በሚገኙ እያንዳንዱ ከተሞች አንድ አንድ ሺህ አባወራዎችን ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የማስፈሩ ስራ እንደሚጠናቀቅ ዶ/ር አበራ ደሬሳ ተናግረዋል።

በሁለተኛውም ዙር በሌሎች የክልሉ ከተሞች የማስፈር ስራውም እንደሚቀጥለና በሶስተኛው ዙር ኑሯቸውን ግብርና ላይ መሰረት ያደረጉ ተፈናቃዮችን ወደተለያዩ ዞኖች ለማስፈር የእርሻ መሬት እየተለየ ነውም ተብሏል።

"ተፈናቃዮቹ ያሉበት ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በአንድ ስፍራ በዝተው የሚገኙትን እና ለተለየ ችግር ተጋላጭ ለሆኑት ቅድሚያ ተሰጥቷል''ብለዋል ዶ/ር አበራ ደሬሳ።

ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ብቻ በከተሞች እና በተለየያዩ ዞኖች እንደሚሰፍሩ የተናገሩት ዶ/ር አበራ ከኦሮሚያ ድንበር አካባቢ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

አጭር የምስል መግለጫ የሞያሌ ተፈናቃዮች

የሀገሪቱ ሕገ-መንግ

የሶማሌ ክልላዊ ብሔራዊ መንግስት አብዲ መሃመድ ኡማር ከሶማሊያ የተፈናቀሉ ግለሰቦች ወደቤት ንብረታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ተፈነቃዮቹ ይመለሱ አይመለሱ በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ አካላት ሲከራከሩ ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 41 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት የሀገሪቱ ዜጎች በሃገሪቱ ድንበር ውስጥ በየትኛውም አካባቢ መኖር እንደሚችሉ ይደነግጋል።

እነዚህን ዜጎች ወደቤት ንብረታቸው ከመመለስ ፈንታ ወደተለያዩ ኦሮሚያ ከተሞችና ዞኖች ማስፈር ይህንን ድንጋጌ ይፃረራል የሚሉት ደግሞ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው።

"የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት የራሱ መንግሥት ይኑረው እንጂ በፌደራል መንግሥቱ፣ በሕገ-መንግሥቱና በአንድ ባንዲራ ስር እስከተዳደረን ድረስ ይህንን ሕገ-መንግሥታዊ መብት በመጣስ ለነዚህ ወገኖች ከቤት ንብረት መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ሰዎችን ለህግ በማቅረብ መንግሥት እነዚህን ተፈናቃዮች ደህንነት አስጠብቆ ወደ ቤት ንብረታቸው የመመለስ ሃላፊነት አለበት። "

"ነገ አንዱ ተነሰስቶ የሌላ አካባቢ ተወላጆችን ቢያፈናቅል ሕገ-መንግሥቱ ይጣሳል። ሀገሪቱም ችግር ላይ ትወድቃለች" ይላሉ አቶ ሙለቱ።

እነዚህን ወገኖች ኦሮሚያ ውስጥ ለማስፈር ከማሰብ አስቀድሞ እንደተጠናና 97% የሚሆኑት ለደህንነታቸው ስጋት ስላደረባቸው ወደ ሶማሌ ክልል መመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው በጥናት ተደርሶበታል ብለዋል ዶ/ር አበራ።

የፌደራል መንግሥቱ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተፈናቃዮቹን ወደ ቤት ንብረታቸው የመመለስ ፍላጎት ቢኖረውም ተፈናቃዮቹ እስካልፈለጉ ድረስ በግድ የመመለስ ስራ እንደማይሰራ ተናግረዋል።

3% የሚሆኑትን ወደ ሶማሌ ክልል ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉም የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ አለመቻል የህግ የበላይነትን ማስከበር አለመቻል ነው ይላሉ አቶ ሙላቱ።

''የእርዳታ ተማፅኖ"

ሕዝቡ ባደረገው ሰፊ ንቅናቄ ተፈናቃዮቹን ያለጉልህ ችግር ማቆየቱ ትልቅ ብርታት ነው ያሉት ዶ/ር አበራ በቁሳቁስ ከተደረገው ድጋፍ ውጭ 441 ሚሊየን ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

ይኹን እንጂ ከተፈናቃዩች ቁጥር እና ለመልሶ ማቋቋሙ ከታቀደው ገንዘብ ጋር ሲነፃፀር አሁንም ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ዶ/ ር አበራ ጠይቀዋል።

የድጋፍ ማሰባሰብ እና መልሶ ማቋቋም ኮሚቴ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በተጨማሪም የተለያዩ ገቢ ማስገኛ መርሃ ግብሮችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ