ለምን ሲሳይ በገና በዓል ለ500 ሰዎች የእራት ምሽት አዘጋጀ

ለምን ሲሳይ Image copyright Hamish Brown
አጭር የምስል መግለጫ ለምን ሲሳይ

የገና በዓል በአብዛኛው ከቤተሰብ ጋር የሚከበር በዓል ነው። የበዓሉን ደስታ አብረው የሚጋሩት ቤተሰብ ከሌለስ?

በማሳደጊያ ውስጥ ያደገው ገጣሚ ለምን ሲሳይ ቤተሰብ በዙሪያቸው የሌለ ሰዎች ገናን ብቻቸውን እንዳያሳልፉ ጥረት እያደረገ ነው።

መኖሪያውን ግሬተር ማንችስተር ያደረገው ታዋቂው ፀሃፊ ለምን ሲሳይ ዓመታዊው የገና በዓል የእራት ግብዣ፤ በብቸኝነት ውስጥ ያሉ ታዳሚዎች መልካም ትዝታ በውስጣቸው እንዲቀር የመተላለፊያ መንገዶችንና የቤቶችን ግድግዳ እንዲዋቡ አድርጓል።

ልጅነቱን በማሳደጊያ ውስጥ ያሳለፈው ለምን በተለይ በእንክብካቤ ማዕከላት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ይህ ወቅት በጣም ከባድ ጊዜ ሊሆንባቸው ይችላል ይላል።

ከማደጎ ልጅነት ወደ እውቅ ገጣሚና የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ሃላፊነት

ብቻቸውን ላሉ ሰዎች የገና በዓል እራትን ከሌሎች ጋር እንዲጋሩ የማድረጉ ሃሳብ የተፀነሰው አንድ በጎ አድራጎት ድርጅት በእንክብካቤ ማዕከላት ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚሰማቸውን የብቸኝነት ስሜት ለመቅረፍ ለንደን ውስጥ ያዘጋቸውን የገና እራት ዝግጅትን ካየ በኋላ ነበር።

''ይህ ዝግጅት እኔ ባለሁበት ማንችስተር ከተማም እንዲካሄድ ፈለግኩኝ፤ ከሃሳቡና በእራሳችን ላይ ከነበረን እምነት ውጪ በእጃችን ላይ ምንም አልነበረንም፤ ቢሆንም ግን አሳካነው" ይላል ለምን።

አጭር የምስል መግለጫ ለምን ሲሳይ የገና እራት ዝግጅቱን ከ4 ዓመት በፊት ነበር የጀመረው

በዚህ ዓመትም 500 ያህል ሰዎች የሚሳተፉበት ተመሳሳይ ዝግጅት በተለዩ የእንግሊዝ ከተሞች ይካሄዳል። እያንዳንዱ ዝግጅትም ዕለቱን እንዴት ማቀድና ማሳካት እንደሚቻል በሚተነትነው በለምን ሲሳይ ተዘጋጅቶ በተሰጣቸው የመመሪያ መፅሃፍ መሰረት በየአካባቢው ባሉ በጉፈቃደኞች ይካሄዳል።

''የገና ዕለትን ለብቻ ማሳለፍ እጅግ ከባድ ነው። በተለይ ወዴትም መሄድ የማይችሉ ወጣቶች ከባድ የብቸኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። ይህ ዝግጅትም በዕለቱ ደስ እንዲላቸውና የሚያስብላቸው ሰው እንዳለ እንዲያውቁ ማድረግ ነው።''

በዚህ ዓመትም የለምን ሲሳይ ፋውንዴሽን የተመዘገበ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ በመመዝገቡ ወደፊት የሚከናወኑት የገና እራት ግብዛዎች እንዳይቋረጡ ያደርጋል።

የተለያዩ ሽልማቶች አሸናፊ የሆነው ፀሃፊ ለምን ሲሳይ ይህንን የበጎ አድራጎት ሥራውን የራሱ ያለፈ ታሪክ አካል አድርጉ ይመለከተዋል። እያንዳንዱን የገና እለት ዕራትም ሁሉም ተሳታፊ ልዩ እንደሆነ እንዲሰማው ለማድረግ ጥረት ይደረግበታል ብሏል።

''ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው የገና ካርድና ደስ እንዲላቸው የሚመረጡት ስጦታዎች ከፍላጎታቸው ጋር እንዲሄዱ በማድረግ ስለእነርሱ የሚያስብ ሰው እንዳለ እንዲረዱ ሁሉ ነገር በጥንቃቄ ይዘጋጃል'' የሚለው ለምን፤ የዚህ የበዓል ዝግጅት ዋነኛ ዓላማ በአጠቃላይ ''የደስታ ስሜትን ለሁሉም እንዲደርስ ማድረግ'' እንደሆነም ይናገራል።

አጭር የምስል መግለጫ ማይክ ሞሪስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እራት ግብዣው የሄደው ባለፈው ዓመት ነበር

ማይክ ሞሪስ ከ13 ዓመቱ ጀምሮ በእንክብካቤ ማዕከል ውስጥ የቆየ ነው። አሁን የ18 ዓመት ወጣት የሆነው ማርክ እንዳለው በገና ብቻውን እንደሚሆን ሲያስብ ''በድብርት ይዋጣል" ግብዣው ላይ ለመገኘት ፍርሃት የነበረበት ቢሆንም ደስተኛ ግን ነበር።

ግብዣውን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ "የእርዳታ ተግባር" አለመምሰሉ ነው ሲልም ይጨምራል። "እርዳታ ለመቀበል የሄድኩ ሳይሆን እዚያ ቦታ ላይ መገኘቴ ትክክል እንደሆነ ተሰምቶኛታል"።

"ወደ ተለያዩ ተቋማት ስሄድ ግን ጠረጴዛው፣ ወንበሩ ሁሉ የሚያስታውሰኝ ሁሌም ድጋፍ ጠባቂ መሆኔን ነው። እዚህ ግን የገና ዛፉ፣ ቤቱ በበዓል መንፈስ አሸብርቋል፤ ሁሉም ሰው ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ነው።"

"ሰዎች ስለእኔ እንደሚጨነቁ እና መጀመሪያ ብቻዬን እንደሆንኩ እንደተሰማኝ እንዳልሆነ እንዲገባኝ አድርጓል።"

"በገና በዓል ልትግባባ ከምትችላቸው ሰዎች ጋር የምታሳልፍ ከሆነ ያ አይደል የገና በዓል መንፈሱ መሆን ያለበት?'' ሲል ይጠይቃል።

አጭር የምስል መግለጫ ሉዊስ ዋልዌይን (በስተግራ) እና ኤማ ሊዊስ-ካሉቦዊላ ማንችስተሩን በአሉን በማዘጋጀት ውስጥ ድርሻ ነበራቸው

ሉዊስ ዋልዌይን እና ኤማ ሊዊስ-ካሉቦዊላ የማንቸስተሩን በዓል የሚያዘጋጀው ቡድን አባል ናቸው።

ኤማ ለምን ሲሳይ ቻንስለር በሆነበት በማንችስተር ዩኒቨርስቲ የምትሰራ ናት፤ በዚህ በዓል ወቅት በአእምሮዋ ውስጥ ትዝታን ጥሎ ያለፈው ነገር በተለያየ የእንክብካቤ ማዕከላት ያሉ እህትማማቶች ሳይታሰብ በግብዣው ላይ መገናኘታቸው ነው።

"ሁለቱም በአሉን ለብቻቸው እንደሚያሳልፉ በሚያውቁ ሰዎች ነው የተመረጡት፤ ነገር ግን እነዚህ እህትማማቾች እዚህ አንደሚገናኙ አያውቁም ነበር" ብላለች።

"ከእኛ ጋር የገና እራትን የተካፈሉበት እለት በዘጠኝ ዓመት ውስጥ ገናን በጋራ ያከበሩበት ብቸኛው እለት ነው።"

ፀሃፊ ተውኔት እና ገጣሚ ሉዊስ በዚህ በዓል ላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ በመሳተፍ በይበልጥ ደግሞ ገቢ በማፈላለግ እና በማሰባሰብ ሥራ ላይ ተሳታፊ ናት።

ይህንን በዓል መልክ ለማስያዝ እሷ በእንክብካቤ መስጫ ተቋማት ውስጥ በነበረችበት ወቅት የነበራትን ልምድ ተጠቅማለች እና በዓሉ በተቋማት ውስጥ ካለው ተቃራኒ እንዲሆን "በተደጋጋሚ ፍተሻ" አካሂዳለች።

በዚህ ዓመት በዋነኛነት የተደረገው ነገር ወደግብዣው ለሚመጡ እንግዶች በአጠቃላይ ታክሲ መዘጋጀቱ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የማንችስተር ከተማ አስተዳደር የገንዘብ ወጪውን ለመሸፈን ተስማምቷል።

"ሰዎች በመምጣታቸው ሀዘን እንዲሰማቸው ሳይሆን እውነተኛ ደስታና ፌሽታ እንዲሰማቸው ነው የምንጥረው " ብላለች ኤማ።

ታዲያ በዚህ ዓመት የማንችስተር እንግዶች በዓሉን የሚያሳልፉት በምንድን ነው?

"የምግብ ዝርዝር ውስጥ የተርኪ ዶሮ አለ በተቻለን መጠን ባህሉን ለመጠበቅ እንሞክራለን"ብላለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ

ተያያዥነት ያላቸው የኢንተርኔት ማስፈንጠሪዎች

ቢቢሲ ለሌሎች የኢንተርኔት ገጾች ኃላፊነት አይወስድም