ጓቲማላ ኤምባሲዋን ከቴልአቪቭ ወደ እየሩሳሌም ልታዛዋውር ነው

Jerusalem Image copyright Reuters

የጓቲማላው ፕሬዚደንት ጂሚ ሞራሌስ እስራኤል የሚገኘው ኤምባሲያቸው ከቴልአቪቭ ወደ እየሩሳሌም እንዲዛወር ትዕዛዝ ሰጡ።

በፌስቡክ ገፃቸው መልዕክቱን ያስተላለፉት ፕሬዚደንት ሞራሌስ እንዳሉት ውሳኔውን ያሳለፉት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር ከመከሩ በኋላ ነው።

ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ አሜሪካ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ እንደሆነች የሰጠችውን እውቅና እንድታነሳ የሚጠይቀውን ውሳኔ በከፍተኛ ድምፅ ሲያሳልፍ ከተቃወሙት ዘጠኝ ሃገራት ጓቲማላ አንዷ ነበረች።

የተባበሩት መንግሥታት ይህንን ውሳኔ ከማሳለፉ ቀደም ብሎ ዶናልድ ትራምፕ ከአሜሪካ ተቃራኒ በመቆም ውሳኔውን የሚደግፉ መንግሥታት ከሃገራቸው የሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚቋረጥባቸው አስጠንቅቀው ነበር።

• ኢትዮጵያ የእየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማነት ከተቃወሙት አንዷ ነች

ሞራሌስ የኤምባሲው ሠራተኞች ለመዘዋወር አስፈላጊውን ክንዋኔ ማካሄድ እንዲጀምሩ ማሳሳባቸውንም ገልፀዋል።

ጓቲማላ ከእስራኤል ጋር የረዥም ጊዜ ወዳጅነት ያላት ሃገር ናት ሲሉም ነው የተደመጡት ፕሬዚደንቱ።

ከአሜሪካ፣ እስራኤልና ጓቲማላ በተጨማሪ ሆንዲዩራስ፣ የማርሻል ደሴቶች፣ ማክሮኔዢያ፣ ናውሩ፣ ፓላዉ እና ቶጎ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆን አለባት ይላሉ።