ከአይኤስ በኋላ የመጀመሪያው ገና በሞሱል እየተከበረ ነው

ሞሱል ከአይኤስ በኋላ ገና እያከበረች ነው Image copyright EPA

አይ ኤስ ከከተማዋ ተጠራርጎ ከወጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የገና ሥነ-ሥርዓት በኢራቋ ሞሱል ከተማ ተከበረ።

አይ ኤስ ከተማዋን በተቆጣጠረበት ወቅት ማንኛውም ዓይነት ክርስትያናዊ በዓላትን ማክበርም ሆነ ዝግጅቶችን ማካሄድ ለሕይወት አስጊ እንደነበረ አይዘነጋም።

አይ ኤስ በከተማዋ የሚገኙ ክርስትያኖችን ወደ እስልምና እምነት እንዲቀየሩ፣ ግብር እንዲከፍሉ ካለሆነ ደግሞ የሞት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ካወጀ በኋላ በርካታ የክርስትና እምነት ተከታዮች አከባባቢውን ለቀው ለመውጣት ተገደው ነበር።

በያዝነው ወር መባቻ የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይደር አል-አባዲ አይ ኤስን ከኢራቅ ለማስወጣት የተካሄደው የሶስት ወር ተልዕኮ በድል መጠናቀቁን አውጀው ነበር።

የሞሱል ከተማ ነዋሪዎች የገና በዓልን በቅዱስ ጳውሎስ ቤተ-ክርስትያን ባከበረቡት ወቅት አካባቢው በታጠቁ ወታደሮች ሲጠበቅ ነበር።

Image copyright EPA

የኢራቅ የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ፓትሪያርክ ሉዊስ ራፋኤል ሳኮ የእምነቱ ተከታዮች በሞሱል፣ በኢራቅ እና በመላው ዓለም ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲጸልዩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፋርካድ ማልኮ አይኤስ ከተሸነፈ በኋላ ወደ ከተማዋ የተመለሰ ክርስትያን ሲሆን የክርስትና እምነትን አንደገና ለማስጀመር ይህ አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብሏል።

በበጎ ፍቃደኞች የተከፈተው ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ-ክርስትያን ለምዕመናን አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛው በሞሱል ከተማ የሚገኝ የክርስቲያኖች ቤተ-እምነት ነው።

አይ ኤስ እአአ በ2014 ሞሱልን ከመቆጣጠሩ በፊት በከተማዋ ውስጥ 35ሺ የሚጠጉ ክርስትያኖች ይኖሩባት ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች