ቱኒዚያ ኢሚሬትስ አየር መንገድ ቱኒዝ እንዳያርፍ አገደች

የኢሚሬትስ አየር መንገድ አውሮፕላን ሲነሳ Image copyright AFP/Getty
አጭር የምስል መግለጫ በቱኒዚያውያን ሴቶች ላይ ተወሰደው እርመጃ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል

በርካታ የቱኒዚያ ዜግነት ያላቸው ሴት መንገደኞች ወደ ተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የሚያቀና የኢሚሬትስ አውሮፕላን ላይ እንዳይሳፈሩ ከተከለከሉ በኋላ ቱኒዚያ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ አየረ መንገድ የሆነውን ኢሚሬትስን በቱኒዚያ እንዳያርፍ አገደች።

ኢሚሬትስ አየር መንግገድ የወሰደው እርምጃ በቱኒዚያ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።

የቱኒዚያ የትራንስፖርት ሚኒስቴር እገዳው ኢሚሬትስ ዓለም አቀፍ ሕግ እና ስምምነቶችን ተከትሎ የበረራ ሥራዎቹን እስኪሠራ ድረስ ይቆያል ብሏል።

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ መንገደኞቹ እንዲዘገዩ የተደረጉት ''የደህንነት መረጃ'' ስለደረሰን ነው ብላለች።

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንዋር ጋርሻ በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት ''እርምጃውን እንድንወስድ ያስገደደንን የደህንነት መረጃ ለቱኒዚያውያን ወንድሞቻችን አካፍለናል'' ብለዋል፤ ለቱኒዚያውያን ሴቶች ከፍተኛ ክብር አለን ሲሉም አክለዋል።

በእንጥልጥል ላይ ያለ ወዳጅነት

የቱኒዚያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ቱኒዚያውያን ሴቶች እንዳይበሩ እንዲሁም በግዛታቸው እንዳያልፉ አድርገዋል።

አርብ ዕለት የቱኒዚያ ባልሥልጣናት ሁኔታውን እንዲያብራሩላቸው የተባባሩት ኤሜሪትስን አምባሳደር በጠየቁ ጊዜ እገዳው ጊዜያዊ የነበረና የተነሳ መሆኑን አሳውቀዋል።

የቱኒዚያ መገናኛ ብዙሃን ቱኒዚያውያን ሴቶች ኤሚሬትስ አየር መንገድን ተጠቅመው ወደ ዱባይ መሄድ እንዳልቻሉ ሲዘግቡ ቆይተዋል።

ኤኤፍፒ የተሰኘው የዜና ወኪልም ቱኒዚያውያን ሴቶች በኤሚሬትስ አየር መንገድ መጠቀም ብዙ ችግር እያስከተለባቸው እንደሆነ ዘግቦ ነበር።

በ2011 በቱኒዚያ የተነሳው ሕዝባዊ አብዮት ሃገሪቱ ከተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጋር ያላትን ግንኙነት ያሻከረው ሲሆን ሰሜን አፍሪካዊቷ ሃገር ይህንን በእንጥልጥላ ላይ ያለ ወዳጅነት ለማጠንከር ስትታትር ቆይታለች።

ቱኒዚያን ከሚያስተዳድረው ጥምር ፓርቲ አንዱ የሆነው ኤናህዳ ፓርቲ ከኳታር ጋር ግንኙነት እንዳለው ይገመታል፤ ኳታር ደግሞ በበኩሏ ሽብርተኝነትን ትደግፋለች በሚል ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ እንዲሁም ባህሬን ጋር ያላት ወዳጅነት መቋረጡ አይዘነጋም።

ተያያዥ ርዕሶች