የሮማው ጳጳስ አለም የስደተኞችን ጉዳይ ቸል እንዳይል ተማጸኑ

Pope Francis prays during a Christmas Eve Mass at St Peter's Basilica in the Vatican. Photo: 24 December 2017 Image copyright AFP/Getty Images

የሮማው ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ በፈረንጆቹ ገና ዋዜማ መላው አለም በስቃይ ላይ ያሉ ስደተኞችን ጉዳይ ትኩረት እንዳይነፍገው ጥሪ አስተላለፉ።

ጳጳሱ የዛሬውን የስደተኞች ሁኔታ ኢየሱስና እናቱ ማርያም ከናዝሬት ወደ ቤተልሄም ከመሰደዳቸውና የሚያስጠጋቸው ከማጣታቸው ጋር አመሳስለውታል።

"የንፁሃንን ደም ማፍሰስ ምንም ከማይመስላቸው መሪዎች ለማምለጠ ብዙዎች ለመሰደድ እየተገደዱ ነው" ብለዋል ጳጳሱ ።

ጳጳሱ የተለመደውን የገና ንግግራቸውን የሚያደረጉት ዛሬ ነው። የ81 ዓመቱ ፖፕ ፍራንሲስ ራሳቸው ቅድመ አያታቸው ጣልያናዊ ስደተኛ እንደነበሩ በገና ዋዜማ በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስትያን ተሰብስቦ ለነበረው ምእመን ተናግረዋል።

"የብዙ ሚሊዮኖችን ግለ ታሪክ ስንመለከት መሰደድን የመረጡ ሳይሆኑ የሚወዷቸውን ትተው መሰደድ ግዴታ የሆነባቸው ናቸው።"ብለዋል።

በመላው ዓለም 1.2 ቢሊዮን የካቶሊክ እምነት ተከታዮችን የሚመሩት ፖፕ ፍራንሲስ ለእንግዶች በየትኛውም አገር ጥሩ አቀባበል ለማድረግ እምነት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

ጳጳሱ ለስደተኞች መከላከል የጵጵስና ዘመናቸው ዋንኛ ጉዳይ መሆኑን ቀደም ሲልም ግልፅ አድርገዋል።

ጳጳሱ ስለ ስደተኞች ይህን እያሉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት አለም ላይ የስደተኞች ቁጥር 22 ሚሊዩን ደርሷል። የማይናማር ግጭትን የሚሸሹ በርካቶች ደግሞ ይህ ቁጥር በፍጥነት እንዲያሻቅብ እያደረጉ ነው።

የገና ዋዜማ በተለያየ የአለም ክፍል በክርስትያኖች ተከብሯል። በቤተልሄምም ክርስትያኖች በተመሳሳይ መልኩ ተሰባስበው ነበር። ቢሆንም ግን በዌስት ባንኳ ከተማ የታየው የምእመናን ቁጥር አነስተኛ ነበር።

ምክንያቱ ደግሞ የዶናልድ ትራመፕ ለእየሩሳሌም በእስራኤል ዋና ከተማነት እውቅና መስጠትን ተከትሎ አካባቢው ላይ ውጥረት መንገሱ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች