በ2017 አስገራሚ ተግባር የፈፀሙ !

ፊታቸውን ላታውቁት ትችሉ ይሆናል፣ ልታውቋቸው ግን ይገባል ሁሉም በ2017 ተፅእኖ ነበራቸው።

Image copyright Facebook/Dallas Zoo/@byHeatherLong/Reuters

በ2017 ማንም ሳይጠብቃቸው አጃኢብ ያሰኘንን ተግባር ከፈፀሙ ሰዎች መካከል የተወሰኑትን ልናስተዋውቃችሁ ነው። ምክንያቱም እንድንደመም ያደረጉን ነበሩና!

ታራና በርክ- '#እኔም' ከተሰኘው ዘመቻ ጀርባ የነበረች ሴት

ታራና በርክ በ2017 በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነትን ካገኘው ዘመቻ ጀርባ ነበረች።

እኤአ ኦክቶበር 15 ተዋናይት አሊሳ ሚላኖ የፊልም ፕሮዲውሰሩን ሀርቪ ዊኒስቴይን በፆታ ጥቃት መጠርጠርን ተከትሎ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችን ለማበረታታት '#እኔም' የሚል የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻ ጀመረች።

ነገር ግን ታራና በርክ ለመጀመሪያ ጊዜ 'እኔም' የሚለውን ቃል ለዘመቻ የመረጠችው ከዓመታት በፊት ሃሽ ታግ በሰዎች ዘንድ የዛሬውን ያህል ሳይታወቅ ነበር።

ታራና በ2006 በፆታዊ ጥቃት የተጎዱ እና በድህነት የሚኖሩ ጥቁር እናቶችና ልጃገረዶችን ለማገዝ ነበር እንቅስቃሴውን የጀመረችው።

'መረበሽ እንጀምራለን'

እውቅና ወደ ታራና መምጣት ጀመረ። የ '#እኔም' እንቅስቃሴ "ዝምታውን ሰባሪዎች" በታይም መፅሔት የዓመቱ ሰው ተብለው ተመርጠዋል።

''የ 'እኔም' ዘመቻ ተመልሶ መምጣት'' ትላለች ታራና ለቢቢሲ "የኔ ትልቁ ግብ ይህ ቅፅበት ሆኖ ብቻ እንዳያልፍ ነው። ይህ በእርግጠኝነት እንቅስቃሴ ነው።"

"ድምፃችንን ማሰማት እንቀጥላለን፤ መረበሻችንን እንቀጥላለን፤ ታሪካችንን መናገር እንቀጥላለን።"

ጆናታን ስሚዝ- በላስ ቬጋሱ ጥቃት ወቅት የ30 ሰዎችን ህይወት አትርፎ በመጨረሻም በጥይት ተመታ

እኤአ ኦክቶበር 1 በላስ ቬጋስ በሺዎች የሚቆጠሩ የሙዚቃ ድግስ ታዳሚዎች ላይ ሲተኮስ ጆናታን ስሚዝ ሌሎችን ለማትረፍ እየሞከረ እያለ አንገቱ ላይ ተመታ። ከአንድ ወር በኋላም ጥይቱ እዛው አንገቱ ውስጥ ነበር።

Image copyright @byHeatherLong/Twitter

ጆናታን ጥይት እንደዝናብ በሙዚቃ ድግስ ተሳታፊዎቹ ላይ ሲዘንብ ከመኪና ጀርባ ሆኖ ተገን በመያዝ ሁለት ሴቶችን ለማዳን እየሞከረ ነበር። ነገር ግን በጥይት ከመመታቱ በፊት 30 ሰዎችን ማትረፍ ችሏል።

አሜሪካ በዘመኗ ሙሉ አይታ ከምታውቀው በመሳሪያ የታገዘ ጥቃት ይኸኛው ትልቁ ነበር። ስቴፈን ፓዶክ ከማንዳላይ ቤይ ሆቴል 32ኛ ፎቅ ላይ ሆኖ በመተኮስ የ58 ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ 546 ደግሞ አቁስሏል። በመጨረሻም ራሱ ላይ ተኩሶ ህይወቱን አጥፍቷል።

"ጥይቱ መውጣት አለበት"

ጆናታን በድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ-ገፁ እንዲህ ብሎ ነበር "በዚህ ቅፅበት ጥይቱ ሊወጣ አይችልም...ጠንካራ ለመሆን እና ወደ ጤንነቴ ለመመለስ እየጣርኩ ነው "

ስለዚያን እለት ምሽትም "በዚህ አሳዛኝ ወቅት ውስጥ ሆኜ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር ሁላችንም ሰዎች መሆናችንን ነው፤ አስፈላጊ በሆነ ወቅትም አንዳችን በሌላችን ላይ መደገፍ እንዳለብን ነው።"

ሔሊ ዲ አብሩ ሲልቫ ባቲስታ-ተማሪዎቿን ከእሳት አደጋ ለማዳን ብላ ሕይወቷን ያጣችው ብራዚላዊት መምህርት

አንድ ሰው ከከተማ ርቃ በምትገኘዋ ጃናኡባ ከተማ ባለ አንድ መዋዕለ ህፃናት ውስጥ ተቀጣጣይ አልኮል እየረጨ እያለ ህንፃውን ከመለኮሱ በፊት መምህርት ሔሊ ዲ አብሩ ሲልቫ ባቲስታ ተጋፈጠችው።

Image copyright Facebook

እኤአ ኦክቶበር 5 ተማሪዎቿን ከጥቃት ለመከላከል ብላ ግለሰቡን ብትጋፈጠውም ሕይቷን ግን አስከፍሏታል።

የ43 ዓመቷ መምህርት ዳሚዮ ሶሬስ ዶስ ሳንቶስን እንዳይገባ ወጥራ ያዘችው። መጨረሻም እሷን ጨምሮ 4 ሕፃናት እና ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ ሞቱ።

"የፅናት ተምሳሌት እና ጀግንነት"

እሳቱን የለኮሰው ግለሰብ የትምህርት ቤቱ ጥበቃ ነበር። ከዓመት እረፍቱ ሲመለስ ከጤንነቱ ጋር በተያያዘ ከሥራ ተሰናበተ። ወደ ትምህርት ቤቱ የሄደው የሕክምና ማስረጃውን ሊሰጥ ቢሆንም እሱ ግን እሳቱን ለኩሷል።

የብራዚል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሚቼል ቴምር ለሄሊ የሀገሪቱን ከፍተኛ ሥራ ለሰሩ የሚሰጠውን ሜዳሊያ ሸልመዋታል። "የተማሪዎቿን ሕይወት ለማትረፍ ስትል የራሷን ሕይወት አሳልፋ የሰጠች ናት፤ የሁላችንንም ልብ የነካ የፅናት ተምሳሌት እና ጀግንነት" ሲሉ አሞግሰዋታል።

ማርከስ ሑችኢንስ- ሳይታሰብ ጀግና የሆነው እና የ 'ዋና ክራይን' የሳይበር ጥቃት ስቆመው

በ150 ሀገራት የሚገኙ 300ሺህ ኮምፒውተሮችን ያዳረሰውን የሳይበር ጥቃት ድንገት የሳይበር ደህንነት ባለሙያው ማርከስ ሐቺንስ አስቁሞታል።

ዋናክራይ የተሰኘውና ክፍያ የሚጠይቀው ቫይረስ እንደ ባንክና ሆስፒታል ያሉ የትልልቅ ተቋማት መረጃን በመቀየር በምላሹ በቢትኮይን ክፍያ እንዲያካሂዱ መጠየቅ ላይ አነጣጥሮ ነበር።

በእንግሊዝ ብሄራዊ የጤና አገልግሎቱን ከሥራ ውጭ አድርጎት የህሙማንን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎም ነበር።

የ22 ዓመቱ ራሱን በራሱ ያስተማረው ሀከር ማልዌሩን ማለትም የቫይረሱን ማከሚያ ዝግ በሆነ ሥርዓት ውስጥ ከሞከረ በኋላ ያልተያዘ የበይነ-መረብ ዶሜን አግኝቶ አስመዘገበው።

"የማሸነፊያው ቁልፍ ተገኘ"

ድንገት ቫይረሱ የመግደያ ቁልፉን ሲነካው ሶፍትዌሩ ክፍያ መቀበያውን ከመጫኑ በፊት ማልዌሩን እንዲከታተለው ብቻ ሳይሆን ለማስቆምም አስቻለው።

ሎስ አንጀለስ መቀመጫውን ላደረገው ክሪፕቶስ ሎጂክ የሚሰራው እና ማልዌር ቴክ በሚል ስም የሚጦምረው ኤናፋሩ ማርከስ መታወቅ አልፈለገም ነበር፤ ነገር ግን ስሞ ሾልኮ ወጣ። ከዚያ በኋላ ያገኘው የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ከጠበቀው በላይ እንደነበር አልካደም።

በአሁን ጊዜ ከሰዎች ኮምፒውተር ላይ ወደ ባንክ ሒሳባቸው የመግቢያ ኮድን የሚለይ ክሮኖስ የተሰኘ ማልዌር ላይ በመሳተፍ ተከሶ በዋስ ተለቆ ይገኛል። በርግጥ መሳተፉን ቢክድም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግን ሀከሮች በማርከስ ዙሪያ አልጠፋ ብለዋል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕን ቲውተርን የሰረዘው ግለሰብ-ባህቲር ዱያስክ

ሁሉም ሰው በዚህ አይስማማም ነገር ግን የቀድሞው የቲውተር ሰራተኛ ባህቲያር ዱያስክ በ2017 ያልተጠበቀ ነገር አደረገ። ሥራው ላይ በነበረበት የመጨረሻ እለት የፕሬዝዳንት ትራምፕ ቲውተርን ዘጋው።

Image copyright Reuters

አንድ የቲውተር ተጠቃሚ ኖቬምበር 3 ለአስራ አንድ ደቂቃ ከቲውተር መጥፋት ወዶት ነበር።

ምርመራው ቀጥሏል

ሁሉም ሰው ግን ደስተኛ አልነበረም። የቲውተር ኃላፊዎች እንዳሉት "ምርመራችንን እንቀጥላለን፤ እንደዚህ አይነት ነገር በድጋሚ እንዳይከሰትም ለመከላለል እንሰራለን፤ እርምጃም እንወስዳለን ብለዋል።"

የ28 ዓመቱ ወጣት 44.6 ሚሊየን ተከታይ ያለውን የትራምፕ ቲውተር አካውንት በስህተት እንደሰረዘው ተናግሯል። "የተወሰኑ መንካት የሌሉብኝን ነገሮች ነካክቼ ነው የተዘጋው"ሲል ገልጧል።

ቢሆንም ግን የፕሬዝዳንት ትራምፕ አንዳንድ ቲውቶች የማህበራዊ ግንኙነት የጥላቻ ንግግር ደንብን የተላለፈ ነው ብሏል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕም በትዊታቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል "በመጨረሻም መልዕክቴ ወጥቶ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ተስፋ አደርጋለሁ" በማለት።

ናናማል አማ የ98 ዓመቷ ጋ አሰልጣኝ

ሕንዳዊቷ ናናማል አማ ሌሎችን ለማነሳሳት በየትኛውም እድሜ ቢሆን እንደማይረፍድ አረጋግጣለች። በ98 ዓመቷም ዮጋ የምታስተምር ሲሆን የማይገመቱ የአካል እንቅስቃሴዎችንም ታደርጋለች።

ከታች ያለው ፎቶ ናናማል በሚያዚያ ወር የተነሳችው ነው።

በሕንድ ደቡባዊ ግዛት ታሚል ናዱ የምትኖረው ባልቴት ተማሪዎቿን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቧንም አነሳስታለች። ቤተሰቦቿ፣ ልጆቿና የልጅ ልጆቿን ጨምሮ ባጠቃላይ ዮጋ ይሰራሉ።

ሳይን ስሚዝ -በአውቶብስ ከተገጨ በኃላ ተነስቶ ወደ ግሮሰሪ ለመጠጣት የገባው ሰው

ሳይመን ስሚዝ ጁን 24 በሬዲንግ ጎዳና ላይ እየተጓዘ እያለ ነበር አውቶቡስ የእግረኛ መንገድ ላይ ወጥቶ የገጨው እና መሬት ላይ ከመውደቁ በፊት በርካታ ሜትሮች የጎተተው።

ቀጥሎ የሆነው ግን የማይታመን ነው።

ሳይጎዳ ተነስቶ አቧራውን ካራገፈ በኋላ ቀጥ ብሎ ወደ ግሮሰሪ ሄደ፤ መጠጥ አዘዘ- አጃኢብ ነው እንጂ ምን ይባላል።

ሳይመን አነስተኛ ጉዳት ያጋጠመው ሲሆን የአውቶቡሱ ድርጅት ምርመራ አካሂዷል፤ ነገር ግን ማንም የታሰረ የለም።

አትላስ- ወደኋላ የሚገለበጠው ሮቦት

በዚህ ዘመን ተፅዕኖ ለመፍጠር ሰው መሆን አያስፈልግም። ወደኋላ የሚገለበጠው ሮቦት- አትላስም ይህንን ያስረዳል።

Image copyright Boston Dynamics

በሕዳር ወር በቦስተን ዳይናሚክስ ውስጥ በሰው ቅርፅ የተሰራው ሮቦት ወደጀርባ መገልበጥ ተማረ።

ዞሎ ተወዛዋዡ ጎሬላ

በ2017 እንዲደንሱ ካነሳሳዎት ነገር መካከል አንዱ ጎሬላው ዞላ ሊሆን ይችላል።

Image copyright Dallas Zoo

የ14 አመቱ ጎሬላ በዳላስ መካነ አራዊት ገንዳ ውስጥ ሲደንስ ተቀርፆ የተለቀቀው ቪዲዮ ልብን የሚያቀልጥ ነበር።

ያዩት ሁሉ ይቀባበሉት እና በተለየያ ሙዚቃና በተለያየ ስልት ይጫወቱት ጀመር።

በርግጠኝነት ዳንሱን ተክኖበታል።