እንግሊዝ የሩሲያ ጦር መርከቦች የውሃ ክልሌን እየተጠጉ ነው አለች

የሩሲያ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, PA

በፈረንጆች ገና በዓል እለት በእንግሊዝ ኖርዝ ሲ አቅራቢያ የሩሲያ የጦር መርከብ በመታየቱ እንግሊዝም የራሷን የጦር መርከብ ለማስጠጋት መገደዷን የእንግሊዝ ባህር ሃይል አስታወቀ።

እርምጃው ብሄራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ነውም ተብሏል። ሩሲያ በጉዳዩ ላይ ምንም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።

ባህር ሃይሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሩሲያ መርከቦች የእንግሊዝን የውሃ ክልል መጣስ መጀመራቸውንም ገልጿል። በተመሳሳይ በቅርቡ የባህር ስር የኢንተርኔት መስመር ላይ ችግር ፈጥራለች በማለት እንግሊዝ ሩሲያን ማስጠንቀቋም ይታወሳል።

ከአንድ ወር በፊት የእንግሊዝ አየር ሃይልና የሀገሪቱ መከላከያ ሃይል ሃላፊ የሆኑት ማርሻል ሰር ስቱዋርት ፒች እንግሊዝና የሰሜን አትላንቲኩ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ የመገናኛ መስመሮችን መጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ተግባር እንደሆነ ገልፀዋል።

ሩሲያ ተሳክቶላት የባህር ስር የኢንተርኔት መስመሩን ማቋረጥ ብትችል ኖሮ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ በፍጥነት ከባድ ውድቀት ይደርስ እንደነበር ሃላፊው ተናግረዋል።

"የባህር ሃይሉ ሩሲያ የባህር ላይ ጥቃት ለማድረስ ከሞከረች የውሃ ክልላችንን ለማስከበር ወደ ኋላ አንልም ምንም አይነት ፀብ አጫሪነትም አንታገስም" ብለዋል ሃላፊው።

እንግሊዝ ህዝቧን ለመከላከልና ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር መቼም ወደ ኋላ እንደማትል ግልፀዋል።