ጆርጅ ዊሃ የላይቤሪያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫን አሸነፈ

ጆርጅ ዊሃ Image copyright AFP

በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ዕጩዎች ከ50 በመቶ በላይ ድምፅ ባለማምጣታቸው ምክንያት በድጋሚ በተደረገው የላይቤሪያ ምርጫ ጆርጅ ዊሃ ምክትል ፕሬዝደንቱን ጆሴፍ ቦዋኪን በመርታት አሸናፊ ሆኗል።

የሁለተኛው ዙር ምርጫ ድምፅ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ መቆጠሩን የገለፀው የላይቤሪያ የምርጫ ኮሚሽን ዊሃ ከ60 በመቶ በላይ ድምፅ በማምጣት ማሸነፉን በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል።

የላይቤሪያ መዲና ሞኖሮቪያም የዊሃን ማሸነፍ ለማክበር በወጡ ደጋፊዎቹ ተጨናንቃ አምሽታለች። "ውድ ላይቤሪያውያን አሁን ምን ዓይነት ስሜት እየተሳመችሁ እንዳለ ይገባኛል" ሲልም በትዊተር ገፁ ላይ ፅፏል።

በሁለተኛው ዙር ምርጫ የመራጮች ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ቢዘገብም ሂደቱ ሰላማዊ እንደነበር ተነግሯል።

በአስረዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ከአሜሪካ ነፃ ወጥተው በመጡ ጥቁር አፍሪካውያን የተቋቋመችው ላይቤሪያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ስታደርግ በ73 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ከጠቅላላው 4.6 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰው ለምርጫ እንደተመዘገበም ታውቋል።

በዓለም ዙሪያ በእግር ኳስ ችሎታው የሚታወቀው ጆርጅ ዊሃና ተቀናቃኙ ጆሴፍ ቦዋኪ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 50 በመቶና ከዚያ በላይ ድምፅ ባለማምጣታቸው ነበር ወደ ሁለተኛ ዙር ለመሄድ የተገደዱት።

የ73 ዓመቱ የላይቤሪያ ምክትል ፕሬዝደንት ጆሴፍ ቦዋኪ ለ12 ዓመታት ያህል በኤሌን ጆሴፍ ሰርሊፍ ምክትልነት ቢያገለግሉም በምርጫ ፉክክሩ ግን ከአለቃቸው ብዙ ድጋፍ ሲያገኙ አልተስተዋለም።

የምርጫው አሸናፊ ከመታወጁ አስቀድሞ ዊሃ "እኔ ከሽንፈት ጋር ተያይዤ አላውቅም። ማሸነፌም የማይቀር ነው" ሲል ተናግሮ ነበር።

የቀድሞው የፒኤስጂ እና ኤሲ ሚላን ተጫዋቹ ዊሃ 2005 ላይ በተደረገው ምርጫ በመጀመሪያው ዙር ጆንሰን ሰርሊፍን ቢያሸንፍም በሁለተኛው ዙር ግን መሸነፉ አይዘነጋም።

ዊሃ 2011 ላይ በተደረገው ምርጫም በምክትል ፕሬዚደንትነት ተዋዳድሮ ፓርቲው ምርጫውን አቋርጦ በመውጣቱ ምክንያት ድል ሳይቀናው ቀርቷል።

የቢቢሲው አሌክስ ዱቫል "ምንም እንኳ የመራጮች ድምፅ አናሳ ቢሆንም ላይቤሪያ ቀስ በቀስ በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር የሚካሄድባት ሃገር እየሆነች ነው" ይላል።