የሶሪያ ህፃናት ጉዳይ እንዳሳሰበው ተመድ ገለፀ

ታካሚ ሕፃናትን ከደማስቆ ማስወጣት ተጀመረ Image copyright ICRC

አንደ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በፅኑ ህመም ምክንያት የሶሪያዋን ደማስቆ ከተማ ምስራቃዊ ክፍል ለቀው እንዲወጡ የተደረጉ ህፃናት በመንግሥትና ታጣቂዎች መካከል መደራደሪያ እየሆኑ ሲሉ ተናገሩ።

በሶሪያ የተመድ ልዩ መልዕክተኛ ጃን ኤግላንድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በህፃናቱ ፈንታ መንግሥት ያሠራቸውን የታጣቂ ቡድን አባላት ለመልቀቅ እንደተስማማ መረጃው አለኝ" ብለዋል።

በጽኑ የታመሙ ሕፃናትን ከደማስቆ ማስወጣት ተጀመረ

ማክሰኞ ዕለት ወደ ደማስቆ እንዲመጡ ከተደረጉት አራት የካንሰር ህመም ተጠቂ ህፃናት በተጨማሪ ረቡዕ ዕለት 12 ታማሚ ህፃናት ከምስራቅ ጉታ አካባቢ እንዲወጡ ተደርገዋል።

ሃሙስ ደግሞ ሌሎች በፅኑ ህመም ላይ ያሉ ሶሪያውያን ህፃንት ከቦታው እንደሚወጡ ታውቋል።

ፅኑ ህመም ላይ ያሉ ሶሪያውያን ህፃናት ከምስራቅ ጉታ አካባቢ የማስወጣት ሥራ መጀመሩን መጀመሪያ ላይ ይፋ ያደረገው 'ሶሪያ-አሜሪካ የህክምና ማህበረሰብ' የተሰኘ ተቋም ነበር።

የማህበሩ አባል የሆኑት ሞሐመድ ካቱብ ለቢቢሲ ሲናገሩ "በርካታ ሰዎች አሁንም ሕይወታቸውን እያጡ በመሆናቸው ቅድምያ ለማን መሰጠት እንዳለበት ሁሉ ከብዶን ነበር" ይላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት መግለጫ እንዳሚያሳየው 400 ሺህ ሰው ከሚኖርባት ምስራቅ ጉታ 12 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው።

በምስራቅ ጉታ የሚገኘው ጃይሽ አል-ኢስላም የተሰኘው ዋናው ታጣቂ ቡድን በይፋዊ የትዊተር ገፁ መንግሥት 29 አባላቱን በመፍታት ለህፃናቱ መለዋወጫ ለማድረግ መስማማቱን መግለፁ አይዘነጋም።

ኤግላንድ እንደሚሉት "አሁን ላይ በቦታው የሚገኙት ህፃናትም ሆኑ ሌሎች ነዋሪዎች በቂ የሆነ የህክምና አቅርቦት የላቸውም።"

ምስራቅ ጉታ "የጦርነት ቀጣና" ተብላ ከተሰየመች ሰንበትበት ቢልም ነገሮች የተባባሱት ከስድስት ሳምነታት በፊት መንግሥትና ታጣቂዎች የለየለት የተኩስ ልውውጥ ከከፈቱ በኋላ ነበር።

ሩስያና ኢራን የባሽር አል-አሳድን መንግሥትን የሚደግፉ ሲሆን ቱርክ በበኩሏ ታጣቂዎችን እንደምትደግፍ ይታወቃል።