2017: ያልተጠበቁ ቁጥሮች የተመዘገቡበት ዓመት

ባለፉት 12 ወራት ማለት ከፈረንጆቹ 2017 መባቻ እስከ መገባደጃው በርካታ ክስተቶች ዓለምን ጎብኝተዋል። እነሆ ከበርካታ ክስተቶች በጥቂቱ ከቁጥሮች ጋር እንመልከት . . .

37,993

ከጥር እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ኃይል ኢራቅ እና ሶሪያ ላይ የጣላቸው ቦምቦችና ሚሳዔሎች ብዛት። ሩስያም በርካታ የጦር መሣሪያ በተጠቀሱት ቦታዎች ብታዘንብም ቅሉ ቁጥሩ ይፋ አልተደረገም። ዋሽንግተን እና ሞስኮ በጥቃቱ የተጎዱ የሰላማዊ ዜጎች ቁጥር ብለው ካሳወቁት በላቀ ደረጃ ሰው ተጎድቷል ቢባልም ተልዕኮው አይ ኤስን ከሞላ ጎደል ከኢራቅና ሶሪያ አስወጥቷል።

127

የተጠቀሰውን ቁጥር ያህል ንቁ እሣተ ገሞራ በኢንዶኔዥያ ይገኛል። ይህም ሃገሪቱን በዓለማችን በርካታ የእሣተ ገሞራዎች ያሉባት ሃገር ያደርጋታል። ወርሃ ኅዳር ላይ ከእሣተ ገሞራዎቹ አንዱ ፈንድቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።

1.7 ሚሊዮን

በአሜሪካው የፊልም ዓለም 'ሆሊውድ' እየተከናወነ ያለውን ፆታዊ ጥቃት በመቃወም '#me too' የተሰኘውን ቃል በመጠቀም የማህበራዊ ሚድያ ዘመቻውን የተቀላቀሉ ሰዎች ቁጥር። በሃገራችን ኢትዮጵያም '#እኔም' በሚል መሪ ቃል በርካቶች ፆታዊ ጥቃትን ሲያወግዙ ተስተውለዋል። ቢያንስ በ85 ሃገራት የሚገኙ ሴቶች በማህበራዊ ሚድያው ዘመቻ መሳተፋቸው ተነግሯል።

ዜሮ

በሰላም ዘርፍ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚዋ የበርማ መሪ ኦንግ ሳን ሱ ኪ በምያንማር ያሉ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ያወገዙበት ክስተት። ምንም እንኳ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መሪዋ በሃገራቸው እየተከናወነ ያለውን ድርጊት እንዲያወግዙ ተፅዕኖ ቢያሳድርባቸውም፤ ሳን ሱ ኪ ይህን ሊያደርጉ አልቻሉም። ይልቁንም ሁኔታውን "ሐሰተኛ ዜና" ሲሉ አጣጥለውታል። የዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ ኃኪሞች ማህበር በ2017 ብቻ 6 ሺህ የሚሆኑ የሮሂንጃ ሙስሊሞች መገደላቸውን ዘግቧል።

812 የእግር ኳስ ሜዳዎች

በፈረንጆቹ 2017 ሐምሌ ወር ላይ ከአንታርክቲክ ላይ የተደረመሰው የበረዶ ግግር። የበረዶ ግግሩ በእግር ኳስ ሜዳ ቢታሰብ 12 የዓለም ዋንጫዎችን በአንድ ጊዜ ማጫወት የሚችል ስፋት ያለው ነው። ሳይንቲስቶች ክስተቱ እየጨመረ ካለው የዓለም ሙቀት መጠን ጋር ተያያዥነት እንዳለው ይናገራሉ።

44 ጊዜ በየቀኑ

ከህንዷ ኒው ደልሂ የሚወጣው ጭስን መተንፈስ በቀን 44 ሲጋራ ከማጨስ ጋር እኩል ነው ሲሉ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዓለም ካሉ 20 በጣም የተበከሉ ከተሞች መካከል አስሩ በህንድ ይገኛሉ።

60 ሚሊዮን የኦሎምፒክ መዋኛ ገንዳ

ሃሪኬን ሃርቪይ የተሰኘው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ 150 ትሪሊዮን ሊትር የሚለካ ውሃ በአሜሪካ ላይ ጥሏል። በነሐሴ ወር በሂዩስተን ቴክሳስ የጣለው ዝናብ ልኬት ከ60 ሚሊዮን የኦሎምፒክ መዋኛ ገንዳዎች ውሃ ጋር እኩል ነው። አንደ የኦሎምፒክ መዋኛ ገንዳ 50 ሜትር ርዝማኔና 25 ሜትር ስፋት ሲኖረው ጥልቀቱ 2 ሜትር ይለካል።