አሜሪካ በሚሳኤል ማምረት ቁልፍ ያለቻቸው የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ላይ ማእቀብ ጣለች

ኪም ጆንግ ሲክና ሪ ፒዮንግ ኮል Image copyright Reuters

አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ምርት ጀርባ ያሉ ዋንኛ ባለስልጣናት ያለቻቸው ኪም ጆንግ ሲክና ሪ ፒዮንግ ኮል ላይ ነው ማእቀብ የጣለችው።

ማእቀቡ አሜሪካ ውሰጥ ምንም አይነት የባለስልጣናቱ የባንክ ሂሳብም ሆነ ሌላ ሃብት እንዳይንቀሳቀስ የሚያግድ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም (ተመድ) ባለፈው አርብ ላደረገችው ሚሳኤል ሙከራ በአፀፋው ሰሜን ኮሪያ ላይ ማእቀብ መጣሉ ይታወቃል።

ሰሜን ኮሪያም ይህ የተመድ ማእቀብ ሙሉ በሙሉ ኢኮኖሚዋን የሚጎዳ እርምጃ እንደሆነ በመግለፅ ነገሩ የጦርነት እወጃም ነው ብላለች።

አሜሪካ የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል ስራ ቁልፍ ሰዎች ያለቻቸው ባለስልጣናት በተለያየ ጊዜ አገሪቱ ሚሳኤል ስትተኩስ ከኪም ጆንግ አን አጠገብ የነበሩ ናቸው።

ባለፉት ጥቂት አመታት ሰሜን ኮሪያ የተለያዩ ሚሳኤሎችን የሞከረች ሲሆን ሙከራዋን በማስከተልም መላ አሜሪካን መምታት የምትችልበት አቅም ላይ ደርሻለው ብላም ነበር።

ማእቀቡ የተጣለባቸው አንዱ ሪ ፒዮንግ ኮል በሩሲያ የተማሩና የቀድሞ የሰሜን ኮሪያ አየር ሃይል ጀነራል ነበሩ። ኪም ጆንግ ሲክ ደግሞ የቀድሞ ሮኬት ሳይንቲስት ነበሩ።

Image copyright KCNA/Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ሪ ፒዮንግ ኮል እና ኪም ጆንግ ኡን

ሁለቱ ባለስልጣናት ተመድ ባለፈው አርብ ማእቀብ ከጣለባቸው 16 ኮሪያዊያን መካከልም ይገኙበታል።

የተመድ ማእቀብ ወደ ሰሜን ኮሪያ ምንም አይነት ነዳጅም ሆነ ድፍድፍ ነዳጅ እንዳይገባ ያግዳል። በርካታ ሰሜን ኮሪያዊያን በውጭ ሃገር ሰርተው ለአገራቸው የውጭ ምነዛሬ የሚያስገኙ ሲሆን ማእቀቡ ግን እነዚህ ሰሜን ኮሪያዊያን በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያስገድዳል።

ከአገሪቱ ምንም አይነት ኤሌክትሮኒክስና ማሽኖች ወደ ሌሎች ሃገራት እንዳይላኩም ማእቀቡ ያግዳል።

በምላሹ ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ እንደዚህ ያለ እርምጃ ለመውሰድ የተገደደቸው በስኬታችን ስለደነገጠች ነው ብላለች።