ሴቶችን ማብቃት ማህብረሰቡን ከችግር ማላቀቅ ነው፡ ወ/ሮ ዱሬቲ ታደሰ

Durettii Taadasaa Dheeressaa Image copyright Duretti Tadesse

ሴቶችን ማብቃት ከቤተሰብ አልፎ ለማህበረሰቡ እና ለሀገር ሁለንተናዊ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው የምትለውን፤ በገጠር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የምትደግፈውን ወ/ሮ ዱሬቲ ታደሰን እናስተዋውቃችሁ።

ወ/ሮ ዱሬቲ ምንም እንኳን ነዋሪነቷን አሜሪካ ዳላስ ብታደርግም የበጎ አድራጎት ድርጅት በማቋቋም በኢትዮጵያ የሚገኙ የገጠር ሴቶችን ህይወት ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች።

ወ/ሮ ዱሬቲ ከሀገር ከወጣች ከ20 ዓመታት በላይ አልፏታል። ሴት በመሆኗ በቀደመ ህይወቷ ብዙ ወጣ ውረዶችን እንዳሳለፈች የምታስታውሰው ወ/ሮ ዱሬቲ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማስቀረት የበኩሏን ለመወጣት ጥረት እያደረገች እንደሆነ ትናገራለች።

የገጠር ሴቶች የሚያልፉበትን የኑሮ ውጣ ውረድ ጠንቅቄ እረዳለሁ ለዚህም ነው በሴት አያቴ ስም የመረዳጃ ማህበር ያቋቋምኩት ትላለች።

''የእናቴ እናት የነበረችው ጨዋቄ ጉተታ የኔ ጀግና የምላት ሴት ነበርች። ጨዋቄ ልክ እንደ በርካታ የገጠር ሴቶች ያለፍላጎቷ በልጅነቷ ከመደሯም በላይ ባለቤቷ ሌላ ትዳር መስርቶ ልጆች ጥሎባት ሄደ'' ስትል ዱሬቲ ትናገራለች።

ይሁን አንጂ አያቷ ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን ጨምሮ ያለማንም ድጋፍ አስተምረው ለትልቅ ደረጃ ያደረሱ ሴት እንደነበሩ ታስታውሳለች። ''በተግባሯ እና ጽናቷ ምክንያት ከእኔም አልፎ ለሌሎችም አርዓያ ስለነበረች በስሟ የገጠር ሴቶች አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ድርጅት አቋቁሜያለሁ'' በማለት ታስረዳለች።

ከ ሺ ቃላት አንድ ተግባር ይበልጣል የምትለው ወ/ሮ ዱሬቲ፤ ድርጅቱ ሙሉ ትኩረቱን የገጠር ሴቶች ላይ በማድረግ ለእነሱ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ያመጣሉ ተብለው በሚታመኑ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ትላለች።

ወ/ሮ ዱሬቲ ስታስረዳ በኦሮሞ ባህል ውስጥ ደበሬ የሚባል የመረዳጃ ስርዓት አለ። ይህን ስርዓት ተከትለን እሰካሁን 144 የሚታለቡ ላሞችን ለድሃ ሴቶች ገዝተን አከፋፍለናል። አንዲት ሴት ከምትታለበዋ ላም ወተት ትጠቀማለች ከዚያም ጥጃዋ አድጋ ጊደር የሚባል ደረጃ ላይ ስትደርስ ደበሬ የሚባለው ባህላዊ ስነ ስርዓት ይከናወናል፤ በዚህም ጊደሯ ለሌላ ድሃ ሴት ትሰጣለች። ይህችም ሴት ጊደሯ በጊዜ ሂደት ውስጥ ወልዳ ከወተቷ ተጠቅማ የተወለደችውን እንደዚያው ለሌላ ደሃ ሴት ስርዓቱን ተከትላ አሳልፋ ትሰጣች በማለት ወ/ሮ ዱሬቲ ትናገራለች።

በዚህ መሃል ግን ወንድ ጥጃ የተወለደ እንደሆነ የሀገር ሽማግሌዎች ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቀው እንዲሸጥ አድርገው የምትታለብ ላም ይገዛሉ በማለት ጭምር ታስረዳለች።

Image copyright Duretti Taddesse
አጭር የምስል መግለጫ የደበሬ ባህላዊ ስርዓት ሲፈጸም

ከዚህ በተጨማሪ የከብት እርባታ እና አያያዝ እንዲሁም ቁጠባን በተመለከተ ተከታታይ ስልጠናዎች እንሰጣለን። እርስ በራሳቸውም የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እናመቻቻለን ስትል ወ/ሮ ዱሬቲ ትናገራለች።

ድርጅቱ በጸሃይ ብርሃን የሚሰሩ መብራቶችን ለ500 አባወራዎች አከፋፍሎ እንደሰጠም ትናገራለች።

ለዚህ ሁሉ ተግባሬ ስንቅ የሆነኝ በምኖርበት አሜሪካ ሀገር ያገኘሁት ልምድ እና ከጎኔ ያሉ ሰዎች የሚያደርጉልኝ ድጋፍ ነው ትላለች።

''መጀመሪያ ከአሜሪካን ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ በውስጤ የነበረው ችግረኛ ህጻናትን መርዳት ነበር። ጥቂት ህጻናትንም አግኝቼ መርዳት ጀመርኩ፤ ሆኖ ግን የምፈልገውን አይነት ለውጥ ማየት አልቻልኩም።''

''ለልጆች የሚደረገው ድጋፍ በቤተሰብ ደረጃ ለውጥ ሲያመጣ አይስተዋልም። ስለዚህም አካሄዳችንን በመቀየር ሴቶችን የማብቃት ሥራ ላይ ትኩረት አደረግን።''

''ወደፊትም ችግረኛ የሆኑ ሴቶችን በማብቃት ከከፋ የምግብ እጥረት እና ድህነት ለማላቀቅ ጠንክረን እንሰራለን'' ብላለች ወ/ሮ ዱሬቲ።