ካለሁበት 16 ፡ 'ጭራሹኑ መጥፎ ነገሮች እንዳይከሰቱ ማድረግ ብችል ደስታዬ ወደር የለውም'

መንበረ አክሊሉ በሬስቶራንቷ Image copyright MENBERE AKLILU
አጭር የምስል መግለጫ መንበረ አክሊሉ በሬስቶራንቷ

መንበረ አክሊሉ እባላለሁ የምኖረው ሪችመንድ፤ ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ ነው።

መጀመሪያ ከኢትዮጵያ ስወጣ ወደ ጣሊያን ሃገር ነበር የሄድኩት። እዚያም ለ13 ዓመታት ኖሬ ሮም ውስጥ እያለሁ ልጅ ወለድኩ። ልጄ 11 ዓመት ሲሆነው፤ የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ በተለይ ደግሞ የአሜሪካን የስኬት ሕልሞች በመመኘት ወደ ካሊፎርንያ አቀናሁ።

ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ ብቻዬን ልጄን አስተምሬ በማሳደግ በተጨማሪም በቻልኩት አቅም ሰዎችን ለመርዳት የቻልኩት እዚህ ስለሆንኩ ነው። በኢትዮጵያዊነቴ እጅጉን ብኮራም አሜሪካ ያደረገችልኝ ግን ቀላል አይደለም።

እዚህ ለሚሠራና ለተማረ ብዙ በሮች ክፍት ናቸው። ከዚያም በላይ ነፃነት የሰፈነባት፣ መብት የሚጠበቅባትና ድምፅን ከፍ አድርጎ ማሰማት የሚቻልባት ቦታ ናት አሜሪካ። በዚህም ከራሴ አልፌ በተለያዩ መንገዶች የተለያዩ ሰዎችን ለመርዳትና ለመደገፍም ችያለሁ።

የትም ቦታ ብሆን የእንጀራን ያህል የሚሆንልኝ ምግብ ባይኖርም፤ ለረዥም ዓመታት ስለኖርኩበትም ሊሆን ይችላል አብልጬ የምወዳቸውና ስመገባቸውም የሚያሰደስቱኝ የጣሊያን ምግቦች ናቸው።

በተለይ ደግሞ የፓስታ ዘር የሆኑ ምግቦችን በሙሉ እወዳለሁ ምክንያቱም ለመሥራት በጣም ቀላል ናቸው። ፓስታ፣ የወይራ ዘይትና ቲማቲም ካለ በቀላሉ የሚጣፍጥ ምግብ ማዘጋጀትና ማጣጣም ይቻላል።

Image copyright Getty Images

ሃገር ቤት ያለው ኑሮ ይናፍቀኛል በተለይ እኔ ባደኩበት ዘመን የነበረው ጉርብትናና ጥምረት። አብሮ መኖሩ፣ ለቡና መጠራራቱ፣ ስኳርም ሆነ ድስት መዋዋሱ፣ ጎረቤት ሄዶ ውሎ ማደሩና እርስ በርስ የነበረው መደጋገፍ በጣም ይናፍቀኛል።

ጣሊያንም ሆነ አሜሪካ ውስጥ ግን እንደዚህ አይነት ማህበራዊ ኑሮ ለመመሥረት ይከበዳል። ልጄን ጎረቤት መላክ ቀርቶ ብዙ ጊዜ ከጎረቤቶቼ ጋር መንገድ ላይ ስንተያይ እንኳን እንደማይተዋወቅ ሰው ነው የምንተላለፈው።

ከቤቴ ቁጭ ብዬ በመኝታ ቤቴም ሆነ በሳሎኔ መስኮት በኩል ከዉሃ ዳር የምትገኘው የኦክላንድ ከተማ ትታየኛለች። ቤትም ሆነ ምግብ ቤቴ ተቀምጬ በምተክዝበት ሰዓት ይህን በዙሪያዬ ያለውን እይታ ስመለከት ዕድለኛ እንደሆንኩ ያስታውሰኛል።

ያም ሆነ ይህ ግን የምኖርበት አካባቢ በጣም ደስ የሚል ነው። በተለይ ከቤቴም ሆነ ከምግብ ቤቴ ሆኜ ወደውጭ ስመለከት ያለው እይታ መንፈሴን ያድሰዋል።

በትክክልም ብዙ ሰው የሚመኘውን 'አሜሪካን ድሪም' የሚባለውን የአሜሪካንን ኑሮ አሳክቻለሁ ብዬም አስባለሁ።

Image copyright MENBERE AKLILU

በቆይታዬ ብዙ የሚያሰደንቁ ነገሮችም አጋጥመውኝ ያውቃሉ። ከሁሉም በላይ ያስገረመኝ አንድ ገጠመኝ ግን ምግብ ቤቴን ላጣ የነበረበት ነው።

በአንድ ወቅት ምግብ ቤቴ ያለበትን ሕንፃ አከራይቶኝ ከነበረው ሰው በ30 ቀን ለቅቄ እንድወጣ የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ ደረሰኝ።

እንዴት እንደሆነ ሳላውቅ የከተማው ከንቲባ ነገሩን ሰምተው ነዋሪውን በማስተባበር መፈክር በመያዝ ለቅቄ እንዳልወጣ ታገሉልኝ እኔም አሸነፍኩ።

በጣም ነበር የገረመኝ፤ ምክንያቱም የሪችሞንድ ከንቲባ የበጎ አድራጎት ሥራዎቼን አውቀው በማመስገን እንዳልፈናቀል መሟገታቸውና ነዋሪውም ለእኔ ያለውን ቦታ በማየቴ እስካሁን እደነቃለሁ።

እዚህ ደረጃ የደረስኩበትን ሂደት መቼም አልረሳም ምክንያቱም ከችግር ነው የተነሳሁት። ጎዳና ተዳዳሪነት የስደት ሕይወቴ አንድ አካል ነበረ ።

በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አልፌ ነበር በሰዓት 7 ዶላር የሚያስገኝ ሥራ አግኝቼ መንገዴን ማስተካከል የጀመርኩት። ከዚያም ቀስ በቀስ እራሴን አሳድጌ ከ16 ዓመታት በፊት የጀመርኩት የምግብ ቤት ሥራ ስኬታማ ሆኖ እዚህ ደርሻለሁ።

ያንን ያለፍኩበትን ሁኔታም በማስታወስ ሌሎችን በቻልኩት ደረጃ ለመርዳት እጥራለሁ።

Image copyright MENBERE AKLILU
አጭር የምስል መግለጫ መንበረ እየከፈለች ከምታስተምራቸው ልጆች ጋር በምግብ ቤቷ ደጃፍ

በዓመት አንድ ቀን 'ቴንክስጊቪንግ' በተሰኘው ትልቁ የአሜሪካ በዓል ወደ 1200 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከየቦታው በአውቶቡስ አሰባስቤ፣ አብልቼ፣ አልብሼ፣ ለዕለት-ተዕለት ኑሯቸው የሚጠቀሙበትን ዕቃና ይዘውት የሚሄዱትንም ምግብ አሰናድቼ ወደሚኖሩበት ቦታ እንሸኛቸዋለን።

የእናቶች ቀን በሚከበርበት ዕለት ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ልጆቻቸውን ያጡ ወይም ብቻቸውን ልጅ የሚያሳድጉ እናቶችን በመሰብሰብ ቢያንስ ለአንድ ቀን ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው እናደርጋለን።

ለዚህ ደግሞ ወደ ውበት ሳሎን ሄደው ከተዋቡ በኋላ ወደ ምግብ ቤቴ መጥተው እንዲጋበዙና ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ቀኑን ደስ ብሏቸው እንዲውሉ አደርጋለሁ።

በተጨማሪም ደግሞ በጣም ጥሩ ውጤት የሚያመጡ ነገር ግን ቤተሰቦቻቸው ለትምህርት ቤታቸው የመክፈል አቅም የሌላቸውን ልጆች ወጪያቸውን እሸፍናለሁ። ትምህርታቸውንም ሲያጠናቅቁ በእነርሱ ቦታ ሌሎች ጎበዝ ተማሪዎችን መርጬ እተካለሁ።

አሁን ለጊዜው በቻልኩት አቅም እየሠራሁ ያለሁት ከቁጥጥሬ ውጪ ሆነው መጥፎ ውጤት ባስከተሉ ነገሮች ዙሪያ ነው። ሆኖም ጭራሹኑ መጥፎ ነገሮች እንዳይከሰቱ ማድረግ ብችል ደስታዬ ወደር የለውም።

ለምሳሌ በሪችመንድ ካሊፎረኒያ የለውን የወንጀል መጠን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባልችልም እንኳን ቢያንስ ቁጥሩን በጣም ዝቅ ማድረግ ብችል እመኛለሁ። ለጊዜው ግን በአቅሜ የምችለውን ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም።

ምክንያቱም እ.አ.አ በ1984 እኔ እራሴ የጎዳና ተዳዳሪ ነበርኩ፤ ከዚያ ከባድ ኑሮ እንድወጣ ያለኝን በሙሉ ዓለም ነው የሰጠኝ ። ስለዚህ ከዓለም ያገኘሁትን ደግሞ ለዓለም መመለስ እንደሚኖርብኝ አምናለሁ።

ይህንንም ለማድረግ አቅሜ ከጠነከረበት ካለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ ያለማቋረጥ ሰዎችን ለመርዳትና አለሁላችሁ ለማለት እጆቼን ምንጊዜም እዘረጋለሁ።

ከሁሉም በላይ የሚያስደስተኝ ግን የሪችመንድ ነዋሪዎች ለእኔ ያላቸው ጥልቅ ፍቅርና አክብሮት ነው። ለምሠራው ነገር በሙሉ ልባቸውን ክፍት አድርገው እርዳታቸውን ለማበርከትም ምንጊዜም ዝግጁ ናቸው።

በቅርቡ ደግሞ የሕንፃ ባለቤት እንድሆን ብዙ ጥረው እዚያው ሐይቁ ላይ ሕንፃው የራሴ የሆነ ምግብ ቤት እንዲኖረኝ ስላደረጉኝ ምስጋናዬ እንዲደርሳቸው እፈልጋለሁ።

ከምኞቶቼ ሁሉ አሁን ቢሆን ደስ የሚለኝ በእናቴ ሃገር ጎጃም በስሟ በሚጠራው በፋንታዬ ተገኘ ሆቴል እራሴን ባገኘው እመኛለሁ።

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገረቻት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦

ካለሁበት 17 ፡ ከሰው አልፎ ለእንሰሳት ቦታ በሚሰጥበት ከተማ ውስጥ ነው የምኖረው

ካለሁበት 18፡ አውስትራሊያ መጥቼ እርቃናቸውን የሚሄዱ ሰዎችን ሳይ በጣም ደነገጥኩኝ

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ