በአፍጋኒስታን በሺዓ ማዕከል በተፈጸመ የሽብር ጥቃት በርካቶች ተገደሉ

የጸጥታ ኃይሎች ከጥቃቱ በኋላ መንግዶችን ዘግተዋል። Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የጸጥታ ኃይሎች ከጥቃቱ በኋላ መንግዶችን ዘግተዋል።

የአፍጋኒስታን መዲና በሆነችው ካበቡል የሺዓ የባህል እና እምነት መዕከል አቅራቢያ በተፈጸመ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ቢያንስ 40 ሰዎች ሲገደሉ 30 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የአፍጋኒስታን የአገር ውስጥ ሚንስትር ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከአጥፍቶ ጠፊው ጥቃት በፊት በአካባቢው ሁለት ፍንዳታዎች ነበሩ ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ እራሱን አይ ኤስ አይ ኤስ ብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን በአፍጋኒስታን የሺዓ ማዕከላት አቅራቢያ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ሲፍጽም ቆይቷል።

ከጥቃቱ በኋላ በማሕበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የበርካታ ሰዎች አስክሬን በጥቃቱ ስፍራ ወድቆ ታይቷል።

የሽብረ ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት በአካባቢው በሚገኙ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ውይይት እያደረጉ ነበር ተብሏል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ሰኞ በአፍጋኒስታን የደህንነት መስሪያ ቤት አቅራቢያ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት 10 ሰዎች ተገድለዋል።

ባሳለፍነው ሰኞም በአፍጋኒስታን የደህንነት መስሪያ ቤት አቅራቢያ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት 10 ሰዎች ሲገደሉ 5 ደግሞ ቆስለዋል።

የሽብር ጥቃቱ ፈጻሚ ወደ ደህንነት መስሪያ ቤቱ በእግሩ በመጠጋት ለብሶት የነበረውን ቦምብ እንዳፈነዳ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ወደ ሥራ በመግባት ላይ የነበሩ የመስሪያ ቤቱ ስራተኞች ይገኙበታል።

ለዚህ ጥቃት የሱኒ ሙስሊም ታጣቂው የእስላማዊ መንግሥት ቡድን ሃላፊነቱን ወስዷል።