እስራኤል አዲስ የምትሰራውን የባቡር ጣቢያ 'ትራምፕ' ብላ ልትሰይም ነው

Donald Trump places his hand on the Western Wall in Jerusalem on 22 May 2017 Image copyright EPA

የእየሩሳሌም ትናስፖርት ሚኒስቴር በእየሩሳሌም ዌስተርን ዋል አቅራቢያ የመሬት ውስጥ ለውስጥ የባቡር መስመር የመዘርጋትና የባቡር ጣቢያውንም 'ትራምፕ' ብለው የመሰየም ፍላጎት እንዳላው ተዘገበ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ይዝራኤል ካትዝ ይህ እየሩሳሌምን በአገራቸው ዋና ከተማነት እውቅና በመስጠታቸው ለትራምፕ የሚገባቸውን ክብር ለማሳየት የሚደረግ እንደሆነም ገልፀዋል።

አሜሪካ ለእየሩሳሌም የእሥራኤል መዲናነት እውቅና ልትሰጥ ነው

ዌስተርን ዋል የእየሩሳሌም የተቀደሰ ክፍልና አይሁዶች እንዲፀልዩበት የሚፈቀድላቸውም ቦታ ነው።

ይህ እቅዱ ይፋ የሆነው የውስጥ ለውስጥ የባቡር መስመር በቀጣዩ ዓመት እንደሚከፈት ከሚጠበቀውና ከቴል አቪቭ ከሚነሳው የፍጥነት መንገድ ጋር የሚገናኝ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።

ሙስሊሞች ሐራም አል ሻሪፍ፤ አይሁዶች ደግሞ ቴምፕል ማውንት ከሚሉት የተቀደሰው ዌስተርን ዋል ጀርባ እስራኤእል ቀደም ሲል ያደረገችው ቁፋሮ በፍልስጤም ተቃውሞ ቀስቅሶ ነበር።

የተባበሩት መንግስታት የቅርስ ጥበቃ ድርጅት የሆነው ዩኔስኮም በተቀደሰችው ከተማ የሚደረገው ቁፋሮና የውስጥ ለውስጥ ባቡር መስመር ዝርጋታ እንደሚያሳስበው ስጋቱን አስታውቆ ነበር።

ሚኒስተሩ ካትዝ ግን ቴል አቪቭን ከእየሩሳሌም የሚያገናኘው መስመር ዝርጋታ የሃገራቸው 'በጣም አስፈላጊው ብሄራዊ ፕሮጀክት' እንደሆነ በግልፅ ተናግረዋል።

በአገሪቱ ባቡር ኮርፖሬሽን የቀረበላቸውን ፕሮጀክት ማፅደቃቸውንም ገልፀዋል።ሁለት ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው የውስጥ ለውስጥ የባቡር መስመር ከምራብ እየሩሳሌም እስከ ምስራቅ እየሩሳሌሙ ዌስተርን ዋል ድረስ የሚዘልቅ ነው።

የባቡር መስመሩም ሁለት ጣቢያዎች እንደሚኖሩት ይጠበቃል።