አፕል ስልኮች በዝግታ እንዲሰሩ በማድረጉ ይቅርታ ጠየቀ

አፕል አይ ፎን 8ትን ይፋ ሲያደርግ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኩባንያው በ2018 ተጠቃሚዎች የስልካቸውን ባትሪ ደህንነት መከታተል የሚችሉበት ሶፍትዌር ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የቆዩ የአይፎን አይነቶችን ሆን ብሎ በዝግታ እንዲሰሩ በማድረጉ የደረሰበትን ወቀሳ ተከትሎ አፕል ይቅርታ ጠየቀ። ኩባንያው ባትሪዎችን እንደሚቀይርና እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 ተጠቃሚዎች የስልካቸውን ባትሪ ደህንነት መከታተል የሚችሉበት ሶፍትዌር ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የቆዩ አይፎኖችን የያዙ ብዙ ተጠቃሚዎች ወደ አዳዲሶቹ እንዲሸጋገሩ ኩባንያው ሆን ብሎ የድሮዎቹ ቀስ ብለው እንዲሰሩ ሳያደርግ እንዳልቀር ቀደም ሲል ብዙዎች ጠርጥረው ነበር።

አፕልም የድሮ ባትሪዎች ያላቸውን ስልኮቹን ሆን ብሎ በዝግታ እንዲሰሩ ማድረጉን አምኗል። ይህን ያደረገው ግን የስልኮቹ ባትሪ እድሜ እንዲረዝም መሆኑን አስታውቋል።

ኩባንያው ድረ ገፁ ላይ የዋስትና ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ባትሪዎች የሚቀይርበትን ሂሳብ ከ 79 ዶላር ወደ 29 ዶላር ዝቅ ማድረጉንም አስታውቋል።

ኩባንያው በደንበኞቹ ዘንድ ምንም አይነት መጠራጠር እንዲፈጠር እንደማይፈልግና እምነታቸውን ለማግኘትም አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግም ተናግሯል።

"በአፕል ኩባንያ የደንበኞች እምነት ማለት ሁሉም ነገር ነው። የደንበኞችን እምነት ለማግኘትና ለመጠበቅ መስራታችንን አናቋርጥም።" የሚል መልእክቱን ኩባንያው በድረ ገፁ ላይ አስፍሯል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አፕል አሜሪካ ውሰጥ ስምንት የተለያዩ ክሶች የተመሰረቱበት ሲሆን በእስራኤልና በፈረንሳይም ተመሳሳይ ክሶች ተመስርተውበታል።

ኩባንያውም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ያረጁ አይፎኖችን ሆን ብሎ ቀስ ብለው እንዲሰሩ ማድረጉን እንዳመነ ይታወሳል።

ስልኩ የሚሰራበትን የአሰራር ሥርዓት እንዴት ማሻሻል ይቻላል?

የአይፎን ስልክ ተጠቃሚ ከሆኑ ይህን መንገድ መከተል ይችላሉ። በመጀመሪያ ሞባይልዎ የኢንተርኔት ግንኙነት እንዳለው ያረጋግጡ። ዋይፋይ ቢጠቀሙ ይመረጣል።

በመጀመሪያ መቼየት (ሴቲንግ) ይግቡ፤ ከዚያም ጀነራል የሚለውን ሲጫኑ- ሶፍትዌር አፕዴት የሚል አማራጭን ያገኛሉ።

ይህንኑ ሲጫኑ ለስልክዎ የተዘጋጀ አዲስ ስሪት ካለ ማሻሻል ይችላሉ። 'ዩር ሶፍትዌር ኢዝ እፕ ቱ ዴት' የሚል መልዕክት ከተመለከቱ ግን ስልክዎ የተሻሻለው አሰራር ስላለው መጠቀምዎን ይቀጥሉ።

የአንድሮይድ ስልክ (ሳምሰንግ እና ሁዋዌ ስልኮችን ጨምሮ) ተጠቃሚ ከሆኑ ደግሞ ስልክዎ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳለው በማረጋገጥ፤ ወደ ሴቲንግ ይሂዱ ከዚያም አባውት ዲቫይስ የሚለውን ይጫኑ ከዚያም ሶፍትዌር አፕዴት የሚለውን ሲጫኑ ለስልክዎ አዲስ ስሪት ካለ ማሻሻል ይችላሉ።

''ዩር ሶፍትዌር ኢዝ እፕ ቱ ዴት'' የሚል መልዕክት ከተመለከቱ ግን ስልክዎ የተሻሻለው አሰራር ስላለው መጠቀምዎን ይቀጥሉ።