በሃገሪቱ የተከሰቱት ቀውሶችና አዲስ አበባ

Image copyright Sean Gallup

በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ለብዙዎች ህይወት መቀጠፍ እንዲሁም በብዙ መቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል።

ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በሀገሪቱ ተንሰራፍተው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች ህይወት መጥፋት እንዲሁም የመማር ማስተማሩን ሂደት ማስተጓጓላቸው ጭምር ችግሩ ምን ያህል ስር እንደሰደደ አመላካች ነው።

በተለይም ከሰሞኑ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ምላሽም የሟቾች ቁጥር እንዲያሻቅብ እንዲሁም ሥርዓቱ ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎችና ትችቶች እንዲያይሉ ምክንያት ሆነዋል።

ከባለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ እነዚህ ሀገር አቀፍ ተቃውሞዎች ቢነሱም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሱ ብዙዎች ይናገራሉ። በተለያዩ ብሔሮችም መካከል ያለው መፈራቀቅና መጠላላትም የሀገሪቷ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን የሚሉ ጥያቄዎች እያስነሱ ነው።

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ግጭት የደረሱ መፈናቀሎችና ሞቶች፣ በተለያዩ ዪኒቨርሲቲዎች ላይ ያጋጠሙ ግጭቶችና የህይወት መጥፋቶች እንዲሁም ተቃውሞችስ በአዲስ አበባ ተፅእኖ መፍጠር ችለው ይሆን? በክልሎች የሚነሱ ጥያቄዎችስ የሀገሪቱ መዲና ነዋሪ ጥያቄዎች ናቸው?

አዲስ አበባ እንዴት ናት?

በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ አካባቢ መኪና አሽከርካሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ተገኘ የሰሞኑ ሁኔታ እንዴት ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "እኛ ምን እናውቀዋለን፤ ብዙ ከውጭ አገር የሚመጡ ሰዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ላይ እየደረሱ ስላሉ ግጭቶች በበለጠ ይነግሩናል" ብለዋል።

የሚሰሟቸው ዜናዎች ለአንዳንዶች መነጋገሪያ ቢሆኑም የከተማው ሁኔታ በተለያዩ ክልሎች ያለው ቀውስ ብዙም ተፅእኖ አልፈጠረም ብለው ያምናሉ።

"ሥራም እንደተለመደው ነው፤ ተማሪውም ይማራል። የንግድ ተቋማትም የተለመደ ሥራቸውን ያከናውናሉ። በተወሰነ መልኩ አዲስ አበባ የሀገሪቱ አካል አትመስልም" ይላሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የአቶ አለማየሁን ሃሳብ የሚጋሩ ሲሆን ህይወት አዳነ የተባለች የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ "ከቀድሞው ጊዜ ለየት የሚያደርገው ምናልባት አንዳንድ ሰዎች ስላለው ሁኔታ ታክሲ ውስጥ ሲያወሩ እሰማለሁ" ትላለች።

ከዚያ ውጭ ግን በምትማርበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብዙዎች ሲወራና የመወያያ ርዕስ አጋጥሟት እንደማያውቅ ጭምር ትገልፃለች።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው ቀውስ ብዙም የተሰማት በማትመስለው አዲስ አበባ አንዳንዶች ኑሮው እንደ ቀድሞው ነው ቢሉም ስጋቱ እንዳለ ግን አልደበቁም።

በአምስት ኪሎ አካባቢ የሚኖሩት ወይዘሮ ወርቅነሽ ደምሴ የተባሉ እናት ሰዎች ቤተ-ክርስቲያን በሚሄዱበት ጊዜ የፀሎት እና ለሰላም የሚደረጉ መማፀኖች እንዳሉ ይናገራሉ።

ምንም እንኳን በተለያዩ ክልሎች በሥርዓቱ ላይ እየተነሱ ያሉትን ጥያቄዎች የአዲስ አበባ ህዝብም በአብዛኛው ይጋራዋል ቢሉም፤ ወገንን የለዩ ግጭቶች ግን "እንደኛ ለተዋለደ፣ ለተዛመደና ለተዋሃደ ህዝብ እንዲህ አይነት ነገር መምጣቱ አሳዛኝ ነው'' በማለት ወ/ሮ ወርቅነሽ ይናገራሉ።

Image copyright MIGUEL MEDINA

ስጋት

በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ የአዲስ አበባን ሕዝብ ማንቀሳስ ችሎ የነበረው ቅንጅት የቀድሞ አባል የነበሩት አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው "አዲስ አበባ ውስጥ ግጭት ላይኖር ይችላል፣ ጥይት ላይተኮስ ይችላል፣ ሰው ላይሞት ይችላል፣ ህዝቡ ግን በውስጡ ሰላም ያለው አይመስለኝም" ይላሉ።

ውጥረቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዳለ የሚገልፁት አቶ ልደቱ አዲስ አባባ የተለያዩ ሕዝቦች መናኸሪያ መሆኗና በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ላይ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ብሔርን መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው እንደዚህ አይነት ግጭቶች አዲስ አበባ ላይ የመፈጠር ዕድላቸው ኢምንት መሆናቸውንም ይናገራሉ።

"ነገር ግን ከተፈጠረ በጣም አደገኛ ነው፤ ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ ይሆናል" በማለት ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

በአፍሪካ የፖለቲካ ፍልስፍና ምሁር የሆኑት ዶክተር ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ እነዚህ ግጭቶች በተለያዩ ክልሎች በመከሰታቸው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሱን የከተማው ነዋሪ ቢያውቁም ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እንዳልተገነዘበ ይገልፃሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ከአቶ ልደቱ አያሌው ጋርም የሚጋሩት የአዲስ አበባ ህዝብ ከብዙ ብሔረሰቦች የተውጣጣ በመሆኑ አሁን እየተፈጠሩ ያሉትን የብሔር ግጭቶች በጎንዮሽ እንዲያየው እንዳደረገም ዶክተር ዮሴፍ ይገልፃሉ።

"የተለመደች አባባል አለች፤ የአዲስ አበባ ልጅ ሰፈር እንጂ ብሔር አይጠየቅም የምትል፤ ምንም እንኳን የብሔርም ይሁን የመደብ ጥያቄ ብዙ አስርት ዓመታትን ቢያስቆጥሩም አብዛኛው የአዲስ አበባ ህዝብ ኢትዮጵያ በሚለው እንጂ በብሔር ራስን የመግለፅ ነገር የለውም። ስለዚህም እየገጠሙ ላሉት የብሔር ግጭቶች አትኩሮትን ነፍጓል" በማለት ዶክተር ዮሴፍ ይናገራሉ ።

ምንም እንኳን አሁን እየታዩ ያሉት ግጭቶች ከማንነት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ቢነገርም ሥርዓቱ ላይም እንደ ፍትህ ማጣት፣ የወጣቱ ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነትም እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎችም እየተነሱ ነው።

ጥብቅ ቁጥጥር

መንግሥት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ማፈንን እንዲሁም ፅንፈኛ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ብዙዎች የሚናገሩ ሲሆን በተለይም እንደ አዲስ አበባ ባሉት ከተሞች የመንግሥት የቁጥጥር መዋቅርም ከሌሎች ከተሞች በበለጠ የጠበቀ መሆኑም ይነጋራል።

"አብዛኛው የፀጥታ ኃይል አዲስ አበባ አለ። የመንግሥት መዋቅር በከተማዋ ስር የሰደደ በመሆኑ ሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ መቆጣጠር ይችላል" በማለት አቶ ልደቱ ይናገራሉ ።

በተለይም ከሌሎች ክልሎች በበለጠ በአዲስ አበባ አንድ ለአምስት የሚባለው የገዢው ፓርቲ መዋቅር ስር የሰደደና የማያፈናፍን መሆኑንም ጭምር አቶ ልደቱ ይናገራሉ።

አዲስ አበባ ለዘመናት የከተማ የተቃውሞዎች እንቅስቃሴ መነሻ የነበረች ስትሆን ከዚያም በኋላ ግን ወደ ሌሎች ክልሎች የመዛመት ባህርይ ነበራቸው።

በ1993 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንዲሁም በ1997 ዓ.ም ከምርጫ ጋር ተያይዞ የተነሳውም ተቃውሞዎች ተጠቃሽ ናቸው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ግን በተለያዩ ክልሎች ተቃውሞዎች ቢነሱም በአዲስ አበባ የተደራጀ እንቅስቃሴ አይታይም። አቶ ልደቱ ለዚህ እንደ ምክንያትነት የሚጠቅሱት ቀደም ባሉት ተሞክሮዎች ህብረተሰቡ ውስጥ የነበሩትን እንቅስቃሴዎችን የሚያደረጁትም የሚመሩትም ተቃዋሚዎች ነበሩ።

"ሌሎች ከተሞች ለአዲስ አበባ ድጋፍ ከመስጠት ጋር ተያይዞ ነው የሚቀሰቀሱት አሁን ደግሞ በተቃራኒው ነው" በማለት አቶ ልደቱ ይናገራሉ።

የ1997 ምርጫን ተከትሎ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ እንደ ምሳሌ የሚያሱት አቶ ልደቱ፤ ከዚያ በኋላ "በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደሌሉ መቆጠር ይቻላል" የሚሉት አቶ ልደቱም ምናልባት የአዲስ አበባም ሁኔታ ከዚያ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ።

አዲስ አበባ Image copyright MIGUEL MEDINA

በዚህ ይቀጥላል ወይ?

በሀገሪቱ ውስጥ የሚታዩት ቀውሶች ወደ አዲስ አበባ ላለመዛመታቸው ምንም አይነት ዋስትና የለም የሚሉት አቶ ልደቱ፤ አዲስ አበባ ውስጥ ቢቀጣጠል ደግሞ የበለጠ አስፈሪ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

"አሁን እየተከሰቱ ያሉት የብሔር ግጭቶች ከቁጥጥር ውጭ ያልወጡትም ችግሩ አዲስ አበባ ላይ ስላልተከሰተ ነው'' ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ ይከሰቱ የነበሩት ተቃውሞዎች በሥርዓቱ ላይ ብቻ የነበሩ ሲሆን፤ አሁን በተለያዩ ቦታዎች እየታዩ ያሉት ግጭቶች ቅርፃቸውና ይዘታቸው ተቀይሯል።

"በህዝብና በመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ በህዝብና ህዝብ እንዲሁም በፌደራልና በክልል መንግሥታትም መካከል ፍጭቶች እየተስተዋሉ ነው። የኃይል አሰላለፉም ተቀይሯል" ይላሉ አቶ ልደቱ።

ምንም እንኳን ህዝቡ ለውጥ እንደሚፈልግ አቶ ልደቱ ቢናገሩም፤ በተደራጀ መልኩ ለውጥ የማምጣት የፖለቲካ ባህሉ እንደሌለም አቶ ልደቱ ይናገራሉ።

"ህዝቡ ለውጥ ይፈልጋል ነገር ግን ለውጥን ከሆነ አካል ነው የሚጠብቀው። በተወሰነ መልኩ መደንዘዝም አለ፤ ይህ አደገኛ ነው። ለውጥ የሚፈልገውም የሚፈራውም ያውነው። ሁሉም ፀጥ ረጭ ብሎ የሚያይበት ሁኔታ ነው ያለው" በማለት አቶ ልደቱ ይናገራሉ።

ለዶክተር ዮሴፍ በከተማዋ ላይ እየተንሰራፋ ያለው ጣራ የነካ የኑሮ ውድነት እንዲሁም ከብሄርና ከማንነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ አብዛኛው የአዲስ አበባ ህዝብ በተለየ መንገድ እንደሚመለከተውም ይናገራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ከአቶ ልደቱ ጋር የሚጋሩት ከ1997 በኋላ የፖለቲካው ምህዳር መጥበቡ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተሜነት (ኮስሞፖሊታን) መሆን ለዚህ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ያምናሉ።