ቤተ-ክርስቲያን ላይ በተፈፀመ ጥቃት በርካቶች ተገደሉ

ቄስ Image copyright Reuters

ከግብፅ መዲና ካይሮ በስተደቡብ በምትገኘው ሄልዋን አካባቢ በኮፕቲክ ክርስቲያኖች ላይ በተፈፀሙ ሁለት ጥቃቶች 12 ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

አስር ሰዎች የተገደሉት አንድ ታጣቂ ወደ ቤተክርስቲያ ለመግባት በሞከረበት ጊዜ ሲሆን ፖሊሶች ዘልቆ እንዳይገባ አድርገውታል።

ከዚህ ጥቃት ከአንድ ሰዓት በኋላ በተመሳሳይ አካባቢ በሚገኝ የአንድ ክርስቲያን መደብር ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከ100 የሚበልጡ ክርስቲያኖች የአይኤስ የግብፅ ቅርንጫፍ እንደሆነ በሚነገርለት ታጣቂ ቡድን ተገድለዋል።

የተፈፀሙትን ጥቃቶች ተከትሎ የፀጥታ ሠራተኞች በዋና ከተማዋ ካይሮ ዙሪያ ኬላዎችን አቁመው ቁጥጥር እያደረጉ ነው።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፀጥታ ባለሥልጣናት ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም በአዲስ ዓመት እና በኮፕት ክርስቲያኖች የገና በዓል ሰሞን ጥበቃ እንደሚያደርጉ አሳውቀው ነበር።

በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ፖሊሶች ጥበቃ እያደረጉ ሳለ ጥርጣሬ የሚያጭር እንቅስቃሴ ከተመለከቱ በኋላ መሆኑን የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ ፖሊሶች በቀረቧቸው ጊዜ ነበር ተኩስ ከፍተው ጉዳቱን ያደረሱት።

ከሟቾቹም መካከል በቤተክርስቲያኑ ጥበቃ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሦስት ፖሊሶች ይገኙበታል። በጥቃቱ ሁለት ሰዎች በፅኑ የቆሰሉ ሲሆን ሌሎች በርካቶች እንደቆሰሉም ተዘግቧል።

የቢቢሲ ዘጋቢ እንደገለፀው አንድ ሟች ላይ ፈንጂ የተገኘ ሲሆን ይህ ደግሞ ይበልጥ ከባድ የሆነ ጥቃት ተቀነባብሮ እንደነበር ያረጋግጣል። ፈንጅውም በጥንቃቄ እንዲከሽፍ ተደርጓል።

ሌላው ታጣቂ አምልጦ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ ከታተቀው ጦር መሳሪያና ቦምቡ ጋር ተይዟል። በአካባቢው በሚገኝ አንድ መደብር ላይ ጥቃት መፈፀሙም ታውቋል።

የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ-ክርስትያን የአገሪቱ ባለስልጣናት ተገቢውን ጥበቃ እንደሚያደርጉ ከማውራት በዘለለ በተግባር እርምጃ አልወሰዱም ሲሉ መውቀሳቸውን የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።

እንደዚህ ያለው ጥቃት ውጥረትን እንደሚያከርም ቤተ ክርስትያኗ ገልፃለች።

ግብፅ ሙስሊሞች ብዙሃን የሆኑባት አገር ስትሆን አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ክርስትያኖቿ አስር በመቶ የሚሆኑት የኮፕቲክ ክርስትና እምነት ተከታዮች ናቸው።

ሚያዝያ ላይ አሌክሳንደሪያና ታንታ በተሰኙ ከተሞች በሚገኙ የኮፕት አብያተ-ክርስትያናት ላይ በተፈፀሙ ጥቃቶች 45 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ግንቦት ላይ ደግሞ ወደ ገዳም እየሄደ የነበረ አውቶቡስ ላይ በተፈፀመ ጥቃት 29 ክርስትያኖች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ጥቅምት ላይ ደግሞ ካይሮ ውስጥ አንድ የኮፕቲክ ቄስ በስለት ተወግተው መገደላቸው ይታወቃል።

ለጥቃቶቹ ሃላፊነት የወሰዱት ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት አለን የሚሉ አክራሪ ሙስሊም ቡድኖች ናቸው።