በኮንጎ ተቃውሞ ሰልፍ ላይ የነበሩ ሰዎች ተገደሉ

በኪንሻሳ የፖሊስን ጥይት ለማምለጥ የምትሸሽ ሴት Image copyright AFP/Getty
አጭር የምስል መግለጫ ፖሊስ በቤተክርስትያን የተሰበሰቡ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ለመበተን ጥይት ተጠቅሟል

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ከስልጣን እንዲወርዱ በመጠየቅ የተቃውሞ ሰልፍ ከወጡ ሰዎች መካከል ቢያንስ ሰባት ተቃዋሚዎች በፖሊሶች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ አስታወቀ።

ፖሊስ ግን ሦስት ሰዎች መሞታቸውንና የሁለቱ ሞት ምክንያት እየተጣራ መሆኑን ገልጿል።

የፕሬዝዳንት ካቢላ ሁለተኛው የስልጣን ዘመን የሚያበቃው በ2016 መጨረሻ ላይ የነበረ ቢሆንም፤ ምርጫ ባለመካሄዱ እና ተተኪ ባለመመረጡ ምክንያት ከአንድ ዓመት በፊት በተደረሰ ስምምነት በ2017 መጨረሻ ከስልጣን ሊወርዱ ተስማምተው ነበር።

የካቶሊክ የሃይማኖት አባቶች ከእሁድ የአምልኮ ፕሮግራም በኋላ የተቃውሞ ሰልፉን የጠሩ ሲሆን የሃገሪቷ ባለስልጣናት ግን ሰልፉን አግደዋል።

ፖሊስ ተቃዋሚዎችን በተሰበሰቡባቸው ስፍራዎች፣ ቤተ ክርስትያንን ጨምሮ ጥይትና አስለቃሽ ጋዝ በመተኮስ በትኗል።

በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ከቤተክርስትያን ውጭ ሁለት ሰዎች በጥይት ተመተው እንደሞቱ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ገልፀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ፍሎረንስ ማርሻል እንዳሉት በኪንሻሳ ከተገደሉት ከሰባቱ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ሰልፈኞችም በካናንጋ ከተማ ተገድለዋል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝዳንት ካቢላ በ2017 ከስልጣን ለመውረድ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር

ከ 120 ሰዎች በላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል ሲሉም ተናግረዋል።

"በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የተጠቀሙት ኃይል" እና " በፀጥታ ኃይሎች መሰረታዊ መብቶችን እና ነፃነቶችን በኃይል ለማፈን የተደረገ " ያሉትን እርምጃም አውግዘዋል።

ፕሬዝዳንት ካቢላ እኤአ ከ2001 ጀምሮ ስልጣን ላይ የነበሩ ሲሆን በ2016 መጨረሻ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን ማብቃቱን ተከትሎ መውረድ ነበረባቸው። ቢሆንም ግን ተተኪ ለመምረጥ መደረግ የነበረበት ምርጫ አልተካሄደም።

ምርጫ መካሄድ ባለመቻሉ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች የተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሲሆን በርካቶችም ሞተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደገለፀው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የነበሩ በርካታ ሰዎች እንደሞቱ ገልጧል።

በካቶሊክ ቤተ ክርስትያን የሽግግር መንግሥት ለመመስረት የተጀመረው የማግባባት ጥረት መንግሥት እና ተቃዋሚዎች የስልጣን ክፍፍል ላይ ባለመግባባታቸው ተቋርጧል።