ኢራን ውስጥ ለተቃውሞ የወጡ አስር ሰዎች ተገደሉ

ተቃውሞ Image copyright AFP

ኢራን ውስጥ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ምክንያት እሁድ ምሽት 10 ሰዎች መገደላቸውን መንግሥታዊው ቴሌቪዥን አስታወቀ።

ቴሌቪዥን ጣቢያው እንደዘገበው "ትናንት ምሽት በነበረው ተቃውሞ በበርካታ ከተሞች ውስጥ በሚያሳዝን ሁኔታ በአጠቃላይ አስር ሰዎች ተገድለዋል'' ብሏል። ተቃውሞው ከተጀመረበት ባለፈው ሃሙስ አንስቶ ቢያንስ 12 ሰዎች ሞተዋል።

የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሃሳን ሩሃኒ ህዝቡ እንዲረጋጋ ቢጠይቁም ተቃውሞው ቀጥሏል።

ፕሬዝዳንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ተቃውሞውን እንደማይታገሱት አስጠንቅቀው ነበር።

ለአራት ቀናት የተካሄዱትን ፀረ-መንግሥት የተቃውሞ ሰልፎችን ተከትልሎ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሩሃኒ ኢራናዊያን ተቃውሟቸውን ለመግለፅ ነፃ ቢሆኑም የሃገሪቱን ደህንነት ግን አደጋ ላይ መጣል የለባቸውም ብለዋል።

ከካቢኔ አባሎቻቸው ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንቱ እንደተናገሩት መፍትሄ የሚሹ ችግሮች እንዳሉ አምነው ነገር ግን አመፁን የሚታገሱት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ከባለፈው ሳምንት ማብቂያ አንስቶ የተከሰተው እንቅስቃሴ ከስምንት ዓመት በፊት በኢራን ተከስቶ ከነበረው ግዙፍ ሕዝባዊ ተቃውሞ በኋላ ያጋጠመ ትልቁ ተቃውሞ እንደሆነ ተነግሯል።

በበርካታ የኢራን ከተሞች ውስጥ ተቃውሞዎች የተካሄዱ ሲሆን የተቃውሞዎቹ አስተባባሪዎች ይጠቀሙባቸዋል የተባሉ የማህበራዊ መገናኛዎች ላይ መንግሥት እገዳን ጥሏል።

የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው 'ኢሪብ' እንደዘገበው ቴሌግራም እና ኢንስታግራም የተሰኙት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ''መረጋጋትን ለማረጋገጥ'' ሲባል በጊዜያዊነት እገዳ እንደተጣለባቸው ገልጿል።

ተቃውሞው በሃገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ የዋጋ ንረትንና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ተከትሎ ነበር የጀመረው። ነገር ግን በበርካታ ስፍራዎች የሀገሪቱን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሆሚኒንና ፕሬዝዳንት ሩሃኒን እንዲሁም ኢራን በአካባቢው የምታደርገውን ጣልቃ-ገብነትን የሚያወግዙ መፈክሮችን በማሰማት ወደ ፖለቲካዊ ተቃውሞ ተቀይሯል።

ክስተቱን ተከትሎም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው ላይ ''ኢራናዊያን በመጨረሻ ገንዘባቸው እንዴት እየተሰረቀ ለሽብር ተግባር እየባከነ መሆኑን ለመገንዘብ በቅተዋል'' ሲሉ አስፍረው ነበር።

የኢራኑ ፕሬዝዳንት በንግግራቸው ላይ የትራምፕን ትችት አጣጥለው ''ኢራናዊያን ለሃገሪቱ መሻሽልን በሚያመጣ ሁኔታ መንግሥትን ለመቃወምና ትችታቸውን ለማቅረብ ሙሉ ነፃነት አላቸው'' ብለዋል።

ተቃውሞዎች ቅዳሜ ዕለትም በበርካታ ቦታዎች ላይ ቀጥለው የነበረ ሲሆን አንዳንድ ቪዲዮዎች ተቃውሞው እሁድም ቀጥሎ እንደነበር አመልክተዋል።

ጥቂት ሰልፈኞች በዋና ከተማዋ ቴህራን ''ሞት ለአምባገነኑ'' የሚል መፈክር በማሰማት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተቃወሙ ሲሆን ፖሊስም በውሃ ሲበትናቸው የሚያሳይ ቪዲዮ የቢቢሲ ፐርሺያ አገልግሎት አግኝቷል።