ላውሮ ኤርሴናል ቼልሲን ይረታል፤ ዩናይትድም ድል ይቀናዋል ሲል ይገምታል

እንደ ላውሮ ግምት ቢሆን ኖሮ ማንችስተር ዩናይትድ አሁን ላይ ከሲቲ አንድ ነጥብ ልቆ ይገኝ ነበር። በእውነታው ግን ሲቲ ከዩናትድ በ15 ነጥቦች ልቆ ተቀምጧል።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የበዓል ሰሞን ጨዋታዎች ቀጥለዋል። ሰኞ ምሽት በሚደረጉ ጨዋታዎች ዩናይትድ በኤቨርተን ሜዳ የሚፈተን ሲሆን አርሴናል ቼልሲን ያስተናግዳል።

ሰኞ

ብራይተን ከቦርንማውዝ

ብራይተንም ሆነ ቦርንማውዝ ባለፈው ሳምንት ካደረጓቸው ጨዋታዎች አዎንታዊ ነጥብ ማግኘት ችለዋል። ብራይተን ከኒውካስል አቻ ሲለያይ ቦርንማውዝ ኤቨርተንን መርታት ችሏል።

ብራይተን በሜዳው ብዙ ጎል የማስቆጠር ልምድ ባይኖረውም ተጋጣሚዎችን ነጥብ ማስጣል ግን ይችልበታል።

የላውሮ ግምት፡ 1 - 1

በርንሌይ ከሊቨርፑል

Image copyright BBC Sport

ሊቨርፑሎች የጎል ዕድል የመፍጠር አቅማቸው እጅግ እየላቀ መጥቷል። ኩቲንሆ፣ ፈርሚንሆ፣ ሳላህና ማኔ አሁን ላይ ያላቸው አቋም በጣም አስደሳች ሆኗል። ቢሆንም የቡድኑ የመከላከል አቅም አስተማማኝ አይደለም።

በርንሌይዎች በሜዳቸው ባደረጓቸው አስር ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻሉት 10 ጎሎችን ብቻ ነው። እኔ ሊቨርፑል ያሸንፋል ብዬ እገምታለሁ።

የላውሮ ግምት፡ 0 - 2

ሌይስተር ከሃደርስፊልድ

ሌይስተሮች ከሊቨርፑል ጋር በነበራቸው ጨዋታ ጥሩ ተፎካክረው ነበር። ክሎድ ፑዬል ቡድኑን ከያዙት በኋላ ሌይስተር ጥሩ ተፎካካሪ መሆንም ችሏል።

ሃደርስፊልዶች በበኩላቸው ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ቢሆንም ከመንሸራተት ተመልሰው ራሳቸውን 11ኛ ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ችለዋል።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 0

ስቶክ ከኒውካስል

ቅዳሜ በነበረው ጨዋታ ቼልሲ ስቶክ ሲቲን 5-0 ረምርሞታል። የስቶኩ ማርክ ሂዩዝ ለቼልሲ ጨዋታ ያሰለፏቸው ልምድ የሌላቸውን ወጣት ተጫዋቾች ነበር።

ኒውካስሎች አሁን ያሉበት አካሄድ ብዙ አስደሳች አይደለም። በታህሳስ ወር ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ብቻ ነው ማግኘት የቻሉት።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 1

ኤቨርተን ከዩናይትድ

Image copyright BBC Sport

ሳም አላርዳይስ ቡድኑን ከያዙት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኤቨርተን ሽንፈት ገጥሞታል፤ በቦርንማውዝ ሜዳ። አላርዳይስ ተጋጣሚ ቡድንን ማጨናነቅ ይችሉበታል። ከቼልሲ ጋር በነበረው ጨዋታም ያየነው ይሄንን ነው።

ዩናይትድ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት አጠናቋል። ራሽፎርድ በርካታ ጨዋታዎችን በማድረጉ ድካም ላይ ነው ያሉት ሞሪንሆ ሉካኩና ኢብራ ጉዳት ላይ በመሆናቸው ምክንያት ወጣቱን እንግሊዛዊ ሊያሰልፉት እንደሚችሉ ይገመታል። ይሄንን ጨዋታም በድል እንደሚያጠናቅቁት እገምታለሁ።

የላውሮ ግምት፡ 0 - 2

ማክሰኞ

ሳውዝሃምፕተን ከክሪስታል ፓላስ

ሳውዝሃምፕተኖች ከዩናይትድ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ጥሩ አቋም ላይ ነበሩ። ፓላሶች ደግሞ ሲቲን ሊያሸንፉበት የሚችሉበትን ዕድል አባክነው አቻ ተለያይተዋል።

ቢሆንም በዚህ ጨዋታ ሳውዝሃምፕተን ይረታል ብዬ እገምታለሁ።

የላውሮ ግምት፡ 1 - 0

ስዋንሲ ከቶተንሃም

Image copyright BBC Sport

ካርሎስ ካርቫሃል የስዋንሲ አሰልጣኝ ሆነው በተሾሙ በመጀመሪያው ጨዋታቸው ድል ቀንቷቸዋል፤ ያውም ከሜዳቸው ውጭ።

የቶተንሃሙ አጥቂ ሃሪ ኬይን በዚህ ጨዋታ ሶስት ጎል (ሃት-ትሪክ) ማስቆጠር ከቻለ ከ71 ዓመታት በኋላ በሊጉ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሃት-ትሪክ የሰራ ተጫዋች ይሆናል።

የላውሮ ግምት፡ 0 - 3

ዌስትሃም ከዌስት ብሮም

ዌስት ሃም በዴቪድ ሞዬስ ዘመን ለውጥ ማምጣት ችሏል። ዌስት ብሮምም ቢሆን አለን ፓርዲውን ከቀጠረ ወዲህ ድል ባይቀናውም የጨዋታ ለውጥ አሳይቷል።

የላውሮ ግምት፡ 1 - 1

ማንችስተር ሲቲ ከዋትፎርድ

Image copyright BBC Sport

ምንም እንኳ በፓላስ ከመሸነፍ ለጥቂት ቢተርፉም ሲቲዎች ያለ ሽንፈት የውድድር ዘመኑን እንደማያጠናቅቁት አስባለሁ። ጋርዲዮላ በተለይ ደግሞ መጋቢት ወር ገደማ ቻምፒየንስ ሊጉን በማሰብ አጥቂውን ክፍል ሊያሳርፉት እንደሚችሉ አስባለሁ።

ሲቲ በአንድ ክለብ ሽንፈትን እንደሚቀምስ ባምንም ዋትፎርድ እንደማይሆን ግን እርግጠኛ ነኝ።

የላውሮ ግት፡ 4 - 0

ረቡዕ

አርሴናል ከቼልሲ

Image copyright BBC Sport

አርሴናል ከቼልሲ ባለፈው የውድድር ዘመን ያደረጉት ጨዋታ ለቼልሲ ዋንጫ ማንሳት ጉልህ ሚና እንደተጫወተ ይታመናል። አርሴናል ቼልሲን 3 - 0 ከረመረመ በኋላ ኮንቴ አሰላለፋቸውን በመቀየር ከዛ በኋላ የነበሩትን 13 ተከታታይ ጨዋታዎች እንዲያሸንፉ ሆነዋል።

አርሴናል በሜዳው ሲጫወት ጥሩ አቋም ያሳያል። እኔም ይሄንን ጨዋታ ያሸንፋሉ ብዬ እገምታለሁ።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 1