ዩኒሴፍ፡ በፈረንጆቹ 2018 መጀመሪያ ቀን ብቻ በኢትዮጵያ 9023 ህፃናት ይወለዳሉ

በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ 48 ሺህ ህፃናት በአንድ ቀን ይወለዳሉ Image copyright MARCO LONGARI

በ2016 በየቀኑ 2600 የሚሆኑ ህፃናት በተወለዱ በመጀመሪያ ቀናቸው ሕይወታቸው ማለፉን የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ያወጣው መረጃ ያሳያል።

በተመሳሳይ ዓመት በኢትዮጵያና ታንዛኒያ ብቻ 136 ሺህ ጨቅላዎች በተወለዱበት ቀን ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን በዚህ አሃዝ መሠረት በጨቅላ ሕፃናት ሞት ኢትዮጵያ አምስተኛ ስትሆን ታንዛኒያ ደግሞ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የጨቅላዎች ሞት መንስዔ ካለጊዜ መወለድ፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ችግርና የሳንባ ምችን የመሳሰሉ በሽታዎች መሆናቸውንም ነው ደርጅቱ ያስታወቀው።

የዩኒሴፍ የደቡብና ምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ለይላ ፓካላ እንደሚሉት "የዩኒሴፍ ዕቅድ ህፃናት ከሰዓታት የዘለቀ፤ ከወራት የላቀ ከመኖር የበለጠ ዕድሜ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።"

"ለዚህ የሚሊዮን ሕፃናትን ማዳን ዕቅድ መሳካት የመንግሥታትንና አጋር ድርጅቶችን ትብብርን እንሻለን" ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል ዳይሬክተሯ።

ዩኒሴፍ እንደሚለው በምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የሚወለዱ ህፃናት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ከሚወለዱ 386 ሺህ ህፃናት 12 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ።

ከተጠቀሰው 12 በመቶ ደግሞ 58 በመቶው በአምስት ሃገራት የሚወለዱ ህፃናት ናቸው። ከእነዚህም ሃገራት ትልቁን ድርሻ የምትይዘው ኢትዮጵያ ናት ይላል ሪፖርቱ።

• ኢትዮጵያ - 9023

• ታንዛኒያ - 5995

• ኡጋንዳ - 4953

• ኬንያ - 4237

• አንጎላ - 3417

Image copyright AFP

ከላይ የተጠቀሱት አሃዛት አበረታች ባይሆኑም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ግን ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን ሞት በመታደግ ደረጃ አመርቂ ውጤት መታየቱን ድርጅቱ ይናገራል።

ምንም አንኳ አፍሪካ የህፃናትን ሞት በመቀነስ ረገድ መልካም ለውጥ ብታመጣም አሁንም በርካታ መከናወን ያለባቸው ሥራዎች እንዳለባቸውም ድርጅቱ ይጠቁማል።

ዩኒሴፍ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት 'ኤቭሪ ቻይልድ አላይቭ' የተሰኘ አዳዲስ ለሚወለዱ ህፃናት እና ወላጆቹ ተደራሽ የሆነ የህክምና አገልግሎት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ፕሮግራም ይፋ ያደርጋል።