ሳዑዲና አረብ ኤሜሬቶች ቫትን ለመጀሪያ ጊዜ መተግበር ጀመሩ

ሳዑዲና አረብ ኤሜሬቶች ቫት መተግበር ጀመሩ Image copyright Getty Images

ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ተጨማሪ እሴት ታክስን (ቫት) ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምሩ የሸቀጥ ሽያጭና አገልግሎት ላይ 5በመቶ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የባህረ ሰላጤው ሃገራት በርካታ አገልግሎትና ሽያጮቻቸው ከግብር ነፃ በመሆናቸው በርካታ የውጭ ሃገር ዜጎች ለሥራ እንደሚሄዱባቸው ይታወቃል።

የነዳጅ ዋጋ መቀንስን ተከትሎ ግን ሃገራቱ ቫትን ተግባራዊ ለማድረግ መገደዳቸው ተሰምቷል።

የተጨማሪ እሴት ታክሱ ተግባራዊ የሚሆነው በፈረንጆቹ የ2018 የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ነው።

በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በአንድ ዓመት ብቻ የሚሰበሰበው የቫት ገቢ ወደ 12 ቢሊዮን ዶላር ድርሃም (3.3 ቢሊዮን ዶላር) እንደሚሆን ይገምታሉ።

የነዳጅ ምርቶች፣ ምግብ፣ አልባሳት፣ ውሃና መብራትን የመሳሰሉ የአገልግሎት ክፍያዎች እንዲሁም የሆቴል አገልግሎት ግብሩ ተግባራዊ የሚደረግባቸው ዘርፎች ናቸው።

ቢሆንም ህክምና፣ ፋይናንስ እና የህዝብ ትራንስፖርት ከግብሩ ውጪ እነደሚሆኑ ታውቋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የባህረ ሰላጤው ሃገራት የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሰባጥሩ ሲወተውት መክረሙ አይዘነጋም።

ሳዑዲ ከጠቅላላ ዓመታዊ ገቢዋ 90 በመቶው የሚመጣው ከነዳጅ ምርቶች ሽያጭ ሲሆን የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ደግሞ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ገቢ ከተመሳሳይ ዘርፍ የሚገኝ ነው።

ሳዑዲ ከዚህ ቀደም ትንባሆና የለስላሳ መጠጦች ላይ ግብር ተግባራዊ ማድረጓ አይዘነጋም። የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ደግሞ የመንገድ ክፍያና ቱሪዝም ላይ ግብር በመጫን ገቢያቸውን አስፍተው ነበር።

ምንም እንኳ ሃገራቱ ቫትን ተግባራዊ ቢያደርጉም ዜጎች አሁንም ምንም ዓይነት የገቢ ግብር እንደማይከፍሉ ይታወቃል።

የተወሰኑት ሃገራት ጉዳዩን ለፈረንጆቹ 2019 በይደር ቢያቆዩትም ቅሉ። ከሁለቱ ሃገራት በተጨማሪ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ኦማንና ኳታር ቫትን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።