የናይጄሪያ ጦር በቦኮ ሃራም ታግተው የነበሩ 700 ሰዎችን ማስለቀቁን ገለፀ

ጦሩ በቦኮ ሃራም ታግተው የተለቀቁ ያላቸውን ግለሰቦች ፎቶ ይፋ አድርጓል Image copyright Nigerian Army
አጭር የምስል መግለጫ ጦሩ በቦኮ ሃራም ታግተው የተለቀቁ ያላቸውን ግለሰቦች ፎቶ ይፋ አድርጓል

የናይጄሪያ ጦር በቅርቡ ባደረገው ዘመቻ በሃገሪቱ ሰሜን ምስራቅ ክፍል በቦኮ ሃራም ታግተው የነበሩ 700 ሰዎችን ማስለቀቁን ገለፀ።

የጦሩ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ቲሞቴ አንቲጋ እንዳሉት ታጋቾቹ በቻድ ሐይቅ ላይ ከሚገኙ ደሴቶች ለቀው የቦርኖ ክፍለ ሃገር ከተማ ወደ ሆነችው ሞንጉኖ ደርሰዋል።

የጦሩን መግለጫ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት ግን አልተቻለም።

የቢቢሲ ዘጋቢ እንዳለው የታገቱት ሰዎች የተለቀቁት በአንዴ ሳይሆን ቀስ በቀስ ሊሆን ይችላል።

እንደጦሩ መግለጫ ከሆነ በቅርቡ በተደረገ 'ዲፕ ፐንች 2' ዘመቻ ቦኮ ሃራምን ማዳከም ተችሏል።

ፕሬዝዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ በአዲስ ዓመት ለህዝባቸው ባደረጉት ንግግር ቦኮ ሃራም ''አከርካሪው ተሰብሯል'' ብለዋል።

Image copyright Nigerian Army
አጭር የምስል መግለጫ የናይጄሪያ ጦር ታግተው የነበሩት ግለሰቦች ገበሬዎች፣ አሳ አስጋሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው እንደሆኑ ገልጧል

በናይጄሪያ ጦር ፌስቡክ ገፅ ላይ ኮሎኔል አንቲጋ 700ዎቹ "ገበሬዎች፣ አሳ አስጋሪዎች፣ እና ቤተሰቦቻቸው ሲሆኑ በግብርና ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ተገድደው ነበር" ብለዋል።

በቅርቡ የተደረገው ዘመቻ "የቦኮ ሃራም መገናኛ ማዕከላቱን፣ ማሰልጠኛ ጣቢያውን፣ ቦምብ መስሪያ ቁሳቁሱን፣ መኪኖቻቸውን እና ቀለባቸውን የያዙ መሰረተ-ልማቶችን ማውደምን ታሳቢ ያደረገ ነበር "

"የማዘዣ ጣቢያው ሙሉ በሙሉ እንዲወድም እና እንዳያንሰራራ፣ ደሴቶቹን ከሌላው አካባቢ በመነጠል እንዲሁም ታግተው የነበሩት እንዲያመልጡ ማድረግ" ችለናል ሲሉ ፅፈዋል።

ኮሎኔል አንቲጋ ከተለቀቁት ግለሰቦች መካከል የቦኮ ሃራም አባላት ሰርገው እንዳይገቡ ጥንቃቄ መደረጉንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከተለቀቁት መካከል ሁለት ሴቶች በጦሩ የሕክምና ማዕከል ውስጥ በሰላም ወልደዋል።

ከስምንት ዓመታት በላይ ቦኮ ሃራም ከ20ሺህ ሰዎች በላይ ገድሏል፤ 2.6 ሚሊዮን ሰዎችን አፈናቅሏል።

ባለስልጣናት ቦኮ ሃራም እየተንኮታኮተ እንደሆነ መግለጫ ቢሰጡም የቦኮ ሃራም ተዋጊዎች ግን ጦሩ ላይ እና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አድርሰዋል።