ደቡብ ኮሪያ ለሰሜን ኮሪያ የእንነጋገር ጥያቄ አቀረበች

የፒዮንግቻንጉ ኦሊምፒክ ማእከል Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በኦሊምፒክ ጨዋታው ለመሳተፍ ብቁ የሆኑት ሁለት የሰሜን ኮሪያ ስፖርተኞች ብቻ ናቸው

በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ሁለተኛ ሳምንት ላይ ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያ በምታዘጋጀው ኦሊምፒክ ላይ መሳትፍ በምትችልበት ሁኔታ ላይ እንዲነጋገሩ ደቡብ ኮሪያ ጥሪ አቀረበች።

አገሪቱ ጥሪውን ያስተላለፈችው ኪም ጆንግ ኡን ደቡብ ኮሪያ በምታዘጋጀው ኦሊምፒክ የሚሳተፍ ልዑክ ለመላክ እያሰቡ እንደሆነ መግለፃቸውን ተከትሎ ነው።

ኪም ጆንግ ኡን ሁለቱ አገራት በጉዳዩ ላይ በአፋጣኝ መወያየት እንዳለባቸውም ገልፀው ነበር።

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንትም ይህን የኪም ጆንግ ኡንን አዎንታዊነት እየተካረረ ያለውን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለማሻሻል እንደሚረዳ እምነታቸውን ገልፀዋል።

ይህ ቢሆንም ግን መገናኛ ብዙሃን ስለ ሁለቱ አገራት የሚዘግቧቸው ነገሮች አገራቱ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መሆናቸውን ነው።

የደቡብ ኮሪያ ሚኒስትር የሆኑት ቾ ማዮንግ ዮን የሁለቱ አገራት ልዑኮች የሚነጋገሩበት ቀን መቆረጡንም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት ውይይቱ የሚደረገው ሁለቱ ኮሪያዎችን በሚያዋስነውና የስምምነት መንደር ተብሎ በሚታወቀው ፓንሙንጆም ነው።

መንደሩ በከፍተኛ ሁኔታ የጦር ኃይል የሰፈረበትም ሲሆን ቦታው ሁለቱ ኮሪያዎች የሚነጋገሩበት እንደሆነ በታሪክም ይታወቃል።

"ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ፊት ለፊት ሰሜን ኮሪያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ በምን መልኩ መሳተፍ እንደምትችል ይነጋገራሉ። ሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይም እንደሚወያዩ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል ሚኒስትሩ ቾ።

ሁለቱ ኮሪያዎች የሚነጋገሩበት ቀንና ቦታ ይፋ የሆነ ቢሆንም ውይይቱ ላይ ማን እንደሚገኝ እስካሁን ምንም የታወቀ ነገር የለም።

የሁለቱ ኮሪያዎች ከፍተኛ ልዑኮች ከዚህ ቀደም ተገናኝተው የተወያዩት እንደ አውሮፓውያኑ 2015 ማብቂያ ላይ የነበረ ሲሆን ውይይቱ ያለምንም ስምምነት ተጠናቋል።

ማክሰኞ እለት በተደረገው የካቢኔ ስብሰባ ላይ የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙን ጃ ይን የኪም ጆንግ ኡንን አስተያየት በአዎንታዊነቱ እንደሚመለከቱት ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደምም አገራቸው የምታዘጋጀው ኦሊምፒክ ወደ ሰላም የሚያመራ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው ነበር። የሚመለከታቸው ሚኒስትሮች የሚጠበቅባቸውን በመስራት የአገራቱ ግንኙነት የሚታደስበት መንገድ እንዲፈልጉም አዝዘዋል።

የሰሜን ኮሪያ ልዑክ አገራቸው በምታዘጋጀው ኦሊምፒክ ላይ እንዲሳተፍ ሁኔታዎች እንዲመቻቹም አሳስበዋል።

ቢሆንም ግን አገራቸው የሰሜን ኮሪያን የኒኩሌር መሳሪያና ሚሳኤል ምርት ግስጋሴ ለመግታት ከሚሰራው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር መተባበሯ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ አስረግጠዋል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ባልተጠበቀ መልኩ በንግግራቸው ለደቡብ ኮሪያ የተለሳለሱት ኪም ጆንግ ኡን

ኪም ጆንግ ኡን በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ንግግራቸው አሜሪካ ላይ ሲዝቱ ለደቡብ ኮሪያ ግን የእንነጋገር ጥያቄ አቅርበዋል።

"አዲሱ ዓመት 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓሏን ለምታከብረው ሰሜን ኮሪያም ሆነ በዚሁ ዓመት ኦሊምፒክ ጨዋታ ለምታዘጋጀው ደቡብ ኮሪያ ልዩ ዓመት ነው" ብለዋል ኪም ጆንግ ኡን።

በሰሜን ኮሪያ የኦሊምፒክ ጨዋታ ተሳትፎ መደሰታቸውን የኦሊምፒክ ጨዋታው አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ሊ ሂ ቢዮም ለደቡብ ኮሪያ ጋዜጦች ተናግረዋል።

"ይህ የአዲስ ዓመት ትልቅ ስጦታ ነው" ብለዋል።

በኦሊምፒኩ ላይ ለመሳተፍ የሚችሉት ሁለት የሰሜን ኮሪያ ተወዳዳሪዎች ብቻ ናቸው። ምንም እንኳ ሰሜን ኮሪያ በኦሊምፒኩ ላይ መሳተፏን ማሳወቅ ያለባት ጊዜ ያለፈ ቢሆንም ስፖርተኞቿ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋባዥነት ሊሳተፉ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ተያያዥ ርዕሶች