ካለሁበት 17 ፡ ከሰው አልፎ ለእንሰሳት ቦታ በሚሰጥበት ከተማ ውስጥ ነው የምኖረው

ሔዋን ወሌ Image copyright Hewan Wole

ስሜ ሔዋን ወሌ ይባላል መኖሪያዬን በኢስታንቡል ቱርክ ነው ያደረግሁት። ከኢትዮጵያ ከወጣሁ ወደ አሥር ዓመታት ሆኖኛል።

በመጀመሪያም ስወጣ የትምህርት ዕድል አጋጥሞኝ ወደ ሞሮኮ ነበር ያቀናሁት። እዚያም ስምንት ዓመታት ኖሪያለሁ። ሥራ እንደጀመርኩም ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ወደ ኢስታንቡል የሚያመጣ አጋጣሚን አግኝቼ ነበር የመጣሁት።

የተመረቅሁት በፋርማሲ ትምህርት ሲሆን አሁን የምሠራው በዚሁ ዘርፍ በሚሠራ ተቋም ውስጥ ነው። በይበልጥ የማተኩረው በፋርማሲ ዲጂታል ማርኬቲንግ ላይ ሆኖ የፋርማሲ ዕቃዎችንና ውጤቶች ሽያጭ የሚመለከት ዘርፍ ላይ ነው።

የእዚህ ሃገር ነዋሪዎች እንደ ሃገሬ ሕዝብ ሰው ወዳድና እንግዳ ተቀባይ ናቸው። ሆኖም ግን ኢስታንቡልን ከአዲስ አበባ ጋር ለማመሳሰል በጣም ይከብደኛል።

Image copyright Hewan Wole
አጭር የምስል መግለጫ ኢስታንቡል በሁለት አህጉራት ላይ የተቀመጠች ብትሆንም ድልድዩ ያገናኛቸዋል

ሁለቱም ከተሞች የራሳቸው ውበትና ግርማ ሞገስ ቢኖራቸውም፤ ኢስታንቡልን ይበልጥ ለየት የሚያደርጋት በሁለት አህጉር ላይ የተቀመጠችው በዓለም ብቸኛዋ ከተማ መሆኗ ነው።

ቦስፎረስ የተሰኘው ወንዝ ኢስታንቡልን በአንድ በኩል በአውሮፓ ላይ ሲያሳርፋት በምሥራቅ በኩል ደግሞ እስያ ላይ ያሳርፋታል። ይህም ደግሞ ከተማዋን በጣም ውብ ያደርጋታል። በተለይ በውሃ የተከበበች መሆኗን እወደዋለሁ።

አዲስ አበባ በብዛት የተለያዩ ፎቆች ግንባታ ላይ ትገኛለች በኢስታንቡል ግን ግንባታው አብቅቶ ከተማዋን የበለጠ ማስዋብ ላይ ናቸው። የተለያዩ ውብ አትክልቶችን የያዙ ብዙ የሕዝብ መናፈሻ ቦታዎች ይገኙባታል።

ከዚያም በተጨማሪም በውሃው ዳርቻ ለእግረኛና ለሳይክል ነጂዎች ታስቦ የተዘጋጁ መንገዶችም አሉ።

Image copyright Hewan Wole
አጭር የምስል መግለጫ የሕዝብ መናፈሻ

ቱርክ የምትታወቅበት አንደኛው ምግብ ኬባብ ወይም ዶነር በመባል የሚታወቀው ነው። እኔም ብሆን በጣም ነው የምወደው።

በተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት ላይ የተለመደ ምግብ ቢሆንም እንኳን ቱርክ የኬባብ መዲና ናት ለማለት አያዳግትም።

ኬባብ የተለያዩ ሥጋዎችን በተለይ የበሬ ሥጋን ለረጅም ሰዓታት አብስለው ከተለያዩ ቅመማት ጋር በማዋሃድ በስስ ቂጣ ጠቅልለው ያቀርቡታል።

ከዚህም በላይ በጣም ስመገበው የሚያስደስተኝ ጣፋጫቸው ነው። ቱርኮች የተለያዩ ጣፋጭ ምግቦችን ይሠራሉ፤ አንዱን ጣፋጭ ከሌላው ማበላለጥ የማያታሰብ ቢሆንም እኔ ግን ባቅላቫ ነው የምወደው።

Image copyright Hewan Wole
አጭር የምስል መግለጫ (በግራ) ባቅላቫ እና (በቀኝ) ዶነር ወይም ኬባብ

ቤተሰቦቼ ቢናፍቁኝም ከሃገር ቤት እየናፈቀኝ የመጣው ቤተ-ክርስቲያን ማሰቀደስ ነው። ምክንያቱም እዚህ የእራስ የሆነ ቤተ-ክርስቲያን ለማግኘት ከባድ ነው።

ሆኖም ሃገሬን ለማሰብና ሃሳቤን ለማሰባሰብ በምፈልግበት ጊዜ በመስኮቴ ወደ ውጪ እመለከታለሁ።

በከተማዋ በርካታ ሕንፃዎች ስላሉ አብዛኛውን ጊዜ ሕንፃ ብቻ ነው የሚታየኝ። ሆኖም ግን የምኖርበት ስፍራ ከፍታ ላይ በመሆኑ በተለይ ሌሊት ያለውን እይታ እወደዋለሁ።

ከተማዋን ምሽት ላይ በመብራት ተውባ ከቤቴ ስለምቃኛት ደስ ይለኛል።

Image copyright Hewan Wole
አጭር የምስል መግለጫ ማታ ማታ በሳሎኔ መስኮት ከተማዋ በመብራት ተንቆጥቁጣ አያታለሁ

እዚህ ከመጣሁ አንስቶ የሚገርመኝ ለእንሰሳት በተለይ ደግሞ ለውሻ ያላቸው ቦታና ክብር ነው። የእንሰሳት ብዙም አፍቃሪ አልነበርኩም፤ አሁን ግን በጣም ትኩረቴን እየሳቡት ነው።

በከተማው ያሉት የመንገድ ላይ ውሾች በደንብ የተመገቡ፣ ውሃም እንደልባቸው የሚያገኙ፣ ሕክምናም የተሟላላቸው እንደሆኑ አያለሁ። ይህ ሁኔታ ይገርመኝም ስለነበር እንዴት ሊሆን እንደቻለ ስጠይቅ መንግሥት ተገቢውን እርዳታ እንደሚያደርግ ሰዎች ነግረውኛል።

በከተማ ውስጥ አሉ ከሚባሉት የሕዝብ መናፈሻዎች መካከል ብዙዎቹ ለውሻ ታስበው የተመቻቹ ናቸው። ይህም ብቻ አይደለም የበለጠ አስገርሞኝ የነበረው በበረዶ ወቅት የገበያ ስፍራዎች በሙሉ የውሾች ማደሪያ መሆናቸው ነው።

ከሰው አልፎ ለእንሰሳ ቦታ የሚሰጥ ከተማ ውስጥ መኖሬ ሁሌም ያስገርመኛል።

Image copyright Hewan Wole

የከተማዋን ውበትና ሁለመናዋን ብወደውም እንኳን፤ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ መቀነስ ብችል ደስ ይለኝ ነበር።

ከተማዋ በሁለት አህጉር ላይ እንደመቀመጧ ነዋሪው በአንደኛው ክፍል እየኖረ በሌላኛው ስለሚሠራ መንገድ ላይ ምንጊዜም ሰው አይጠፋም።

በመጓጓዣ በኩል ሜትሮ (የመሬት ውስጥ ባቡር) ስላለ በዙ አልቸገርም፤ ቢሆንም በሥራና በትምህርት ቤት መግቢያና መውጫ ሰዓታት ላይ መንገዶች በሙሉ ይዘጋጋሉ።

እንደዚያም ሆኖ ግን ለኢስታንቡል ያለኝን ፍቅር አይቀንስም። በተለይ በዚህ ወቅት ያለው ቅዝቃዜ ግን ከባድ ስለሆነ ምቾት አይሰጠኝም ።

ሕዝቡ ለሰዉ ፍቅር ስላለው ብዙ ነገር ቀሎኝ ነው የምኖረው። ዕድለኛ ሆኜ የማውቃቸው ሰዎችም መልካሞች ስለሆኑ በኢስታንቡል መኖርን ቀላል አድርገውልኛል።

ምንም ቢሆን እናትን የሚያክል ነገር ስለሌለ፤ ብችል በቅጽበት እናቴ ጉያ ውስጥ እራሴን ባገኝ እመኛለሁ።

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገረቻት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦

ካለሁበት 18፡ አውስትራሊያ መጥቼ እርቃናቸውን የሚሄዱ ሰዎችን ሳይ በጣም ደነገጥኩኝ

ካለሁበት 19፡ እንጀራ ማግኘት የማይታሰብባት ከተማ - ሌጎስ

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ