ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለፍልስጤማውያን የሚሰጠው እርዳታ ሊቋረጥ ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለፍልስጤማውያን የሚሰጠው እርዳታ ሊቋረጥ ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ

አሜሪካ ለፍልስጤማውያን የእርዳታ እጇን መዘርጋት ልታቆም ትችላለች። "ስለ ሰላም ለመነጋገር ፈቃደኛ አይደሉም" ብለዋል ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቲውተር መልዕክታቸው አሜሪካ ለምትሰጠው እርዳታ "ምስጋናም ወይንም አክብሮት" ተቀብላ አታውቅም ሲሉም አክለዋል።

በተጨማሪም አጨቃጫቂውእየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት ውሳኔ ለሰላም ድርድሩ "ከጠረጴዛው ላይ መነሳት" ሰበብ ሆኗል።

ፍልስጤማውያን ውሳኔው የሚያሳየው አሜሪካ ገለልተኛ ሆና ልትሸመግል እንደማትችል ነው ብለዋል።

ባለፈው ወር ውሳኔው በተባበሩት መንግሥታት የተኮነነ ሲሆን 128 ሃገራትም ከትራምፕ ውሳኔ በተቃራኒው ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምን አሉ?

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለፓኪስታን የእርዳታ ገንዘብ የላኩትን "ውሸት እና አለመታመን" የሚል የቲውተር መልዕክታቸውን ተከትለው "እንዲሁ በባዶ ቢሊየን ዶላር የምንሰጠው ለፓኪስታን ብቻ አይደለም።"

"በየዓመቱ ለፍልስጤማውያንም በርካታ ሚሊየን ዶላሮች እንሰጣለን ነገር ግን ክብርም ሆነ ምስጋና አላገኘንም። ከእስራኤል ጋር እንኳ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ስለሰላም ለመነጋገር አይፈልጉም" ብለዋል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኒኪ ሃሌይ በተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት

"የድርድሩ አካል የነበረችውን እየሩሳሌም ከጠረጴዛ ላይ አንስተናታል፤ ነገር ግን እስራኤል ለዚያ የበለጠ ትከፍላለች። ፍልስጤማውያን ግን ለሰላም ንግግሩ በራቸውን ዘግተዋል። ታዲያ ለምን ወደፊት ያንን ያህል ገንዘብ እንሰጣቸዋለን?"

ፍልስጤማውያን ምን አሉ?

እየሩሳሌም በዓለማችን በጣም አጨቃጫቂ ከሆኑ ቦታዎች አንዷናት።

እስራኤል ሙሉ እየሩሳሌምን ለዋና ከተማነት ትጠይቃለች። ፍልስጤማውያን ግን በ1967ቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በእስራኤል የተያዘውን ምሥራቅ እየሩሳሌምን የወደፊቷ የፍልስጤም ዋና ከተማ እንድትሆን ይፈልጋሉ።

ትራምፕ ግን ይህ ውሳኔ በቀጠናው አለመረጋጋት ሊፈጥር ይችላል እየተባለ ባለበት እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን በይፋ ተቀብለዋል።

በተጨማሪም የአሜሪካ ኤምባሲም የሁሉም ሃገራት ቆንሲላዎች ካሉበት ቴላቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም ይዞራል ብለዋል።

ከዚህ መግለጫ በኋላም የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሃሙድ አባስ ከትራምፕ መንግሥት የሚመጣ ምንም አይነት ምክረ ሃሳብ አንቀበልም ሲሉ አስታውቀዋል።

እየሩሳሌምንም "የፍልስጤማውያን ዘላለማዊ ከተማ" ብለዋታል።

የትራምፕ ቲውተር መልዕክት የመጣው በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ከሆኑት ኒኪ ሀሌ አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ለፍልስጤማውያን ስደተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ ታቋርጣለች የሚለውን ንግግር ተከትሎ ነው።

ድርጅቱ ትምህርትን፣ ጤናን እና ሌሎች ማህበራዊ ፕሮግራሞችን ያካሄዳል።

አሜሪካ በ2016 ወደ 370 ሚሊየን ዶላር በመስጠት ትልቋ ለጋሽ ሃገር ናት።