"የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መፈታት በውጭ መንግሥታትና ተቋማት ተፅዕኖ አይደለም"

ቃል-አቀባይ መለስ አለም Image copyright MoFA

ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ በእስር ላይ የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ለመፍታት መወሰኑን አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት የተገለፀው በማንም ተፅዕኖ እንዳልሆነ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገለፁ።

የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መፈታትን አስመልክቶ ከውጭ ሀገር የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እነ 'አምነስቲ ኢንተርናሽናል' ኢንዲሁም ምዕራባውያን ሃገራት ጫና በማድረሳቸው ነው ወይ የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል-አቀባይ አቶ መለስ አለም ቀርቦላቸዋል።

"በውጭ ተቋማትና መንግሥታት ተፅዕኖ የተደረገ አዲስ ለውጥ የለም" በማለት አቶ መለስ አለም የተናገሩ ሲሆን "በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ የሚወሰዱ እርምጃዎች በሙሉ የኢትዮጵያ ሕዝብን ታሳቢ ያደረጉ እንጂ በሌሎች ተፅዕኖ የመጡ አይደሉም፤ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነትም ላይ የተለየ ተፅዕኖ የላቸውም" ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 'ኢትዯጵያ በዓለም አቀፍ ግንኙነት የደረሰችበትን የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ደረጃን' በተመለከተ ሳምንታዊ መግለጫ ዛሬ በሰጠበት ወቅት ነው ቃል-አቀባዩ ይህንን የተናገሩት።

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላትና የአሜሪካ ሴኔት ኢትዯጵያ ውስጥ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ የሚደርሱ እሥራት፣ እንግልቶችና ግድያዎች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ በተደጋጋሚ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።

በተለይም ባለፉት ወራት ከተነሱት ሀገራዊ ተቃውሞዎች ጋር እንዲሁም ለ17 ቀናት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የነበረውን ዝግ ስብሰባ ተከትሎ የተሰጡ ውሳኔዎች፤ ከምዕራባውያን ሃገራት ግንኙነት ጋር የፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ወይ ተብሎ ለተጠዩቁት ጥያቄም "ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በሶማሊያ መረጋጋት ላይ ባላት ሚና እንዲሁም በደቡብ ሱዳንና በቀጠናውም እየፈጠረችው ካለው የፖለቲካ መረጋጋትና የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ መሆኗ ሰላም ሳይኖራት ሲቀር በምዕራባውያን በኩል ስጋት እንዲሁም ሊያስጨንቃቸው እንደሚችል" አቶ አለም ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያ መረጋጋት ለአካባቢው ሰላም ከፍተኛ ሚና አለው፤ በወዳጆቻችን በኩል የሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የበለጠ እንዲጠበቅ፣ ዲሞክራሲው ሥር እንዲሰድ የፖለቲካው ምህዳሩ የበለጠ እንዲሰፋ ፍላጎት አላቸው" ብለዋል።

በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ለቀረበላቸውም ጥያቄም ካይሮ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ከ30 በላይ ለሚሆኑ የጉዞ ሰነድ መሰጠቱን ተናግረዋል። ከዓለም አቀፉ የስደተኝነት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ጋር በመሆን ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱበትበን ሁኔታ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያ አዳዲስ ኤምባሲዎችን እየከፈተች ሲሆን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ከማጠናከር በተጨማሪ ብዙ ኢትዮጵያውያን ባሉበትም ኤምባሲዎችና ቆንስላዎችን መክፈቷ የህዝቡን ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተናገሩት አቶ አለም ነገር ግን ባለው የበጀት እጥረት ሳቢያ ኢትዮጵያዊ ባለበት ሁሉ ኤምባሲም ለመክፈት አቅሙ እንደሌለ ገልፀዋል።

በተጨማሪም አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን መግለጫዎችንና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡም በተጨማሪ ጠይቀዋል።

ተያያዥ ርዕሶች