እስራኤል በቅድመ ታሪክ ወቅት የነበረን ስፍራ አገኘች

Stone tools from Jaljulia near Tel Aviv Image copyright Tel Aviv University
አጭር የምስል መግለጫ በመቶዎች የሚቆጠሩ መቁረጫዎች ተገኝተዋል

ከ500 ሺህ ዓመት በፊት አዳኞች የሚጠቀሙበትን እና "ገነት" ተብሎ የተሰየመን የቅድመ-ታሪክ ቦታን ቴል አቪቭ አቅራቢያ ማግኘታቸውን የእስራኤል አርኪዮሎጂስቶች አስታወቁ።

በጃልጁሊያ አቅራቢያው ከሚገኝ አውራ ጎዳና ቀጥሎ በሚገኘው በዚህ ስፍራ በመቶዎች የሚቆጠሩ መቁረጫዎች እና ሌሎች መገልገያ መሣሪያዎች ተገኝተዋል።

አካባቢው የውሃ ምንጭ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ብዛት ያላቸው እንስሳት የሚኖሩበት ስለነበር ለቀደመት ሰዎች መኖሪያነት ትክክለኛ ቦታ መሆኑን ባለሙያዎች አስታውቀዋል።

የቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ አርኪዮሎጂ ኃላፊ ራን ባራኪ እንዳሉት ቦታው "በሚያስደንቅ ሁኔታ ተጠብቆ ቆይቷል።"

"ቦታው እንደ ገነት በመሆኑ ሠዎች ወደዚህ በተደጋጋሚ ይመጣሉ" ሲሉ ገልጸዋል።

Image copyright Tel Aviv University
አጭር የምስል መግለጫ ቦታው በጃልጁሊያ አቅራቢያ ከሚገኝ አውራ ጎዳና ቀጥሎ ይገኛል

"ውሃ፣ ለመሣሪያነት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ለመስራት የሚያስችሉ ድንጋዮችን ይዘው ይመጣሉ። በተጨማሪም ለአደን የሚሆኑትንም እንስሳት ይስባል። የቅድመ ታሪክ ሠዎች ሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሙሉ ይዟል" ብለዋል።

ቦታው ጃልጁሊያ እና ሩት 6 አውራ ጎዳና መካከል ከመሬት በታች አምስት ሜትር ያህል ርቆ ነው የተገኘው። ግኝቱ እንደሚያሳየው ቦታውን ሆሞ ኢሬክተስ በሚባለው የሠው ዝርያ ጥቅም ላይ ይውል ነበር።

Image copyright Tel Aviv University
አጭር የምስል መግለጫ ስፍራው ከመሬት በታች አምስት ሜትር ያህል ርቆ ነው የተገኘው

ምርምሩን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ያካሄደው የእስራኤል የቅርስ ባለስልጣን ግኝቱ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ተጨማሪ ፍንጭ የሚሰጥ ነው ሲል ገልጿል።

አርኪዮሎጂስቶች በአካባቢው ላይ ትኩረት ያደረጉት ባለፈው ዓመት በአዲስ ግንባታ ምክንያት ስፍራው ከታወቀ በኋላ ነው።

ሆሞ ኢሬክተስ ሙሉ ለሙሉ ቆሞ መሄድ የቻለ የሰው ዝርያ ነው። ከዘመናዊው ሰው ተለቅ ያሉና ጠንካሮች ቢሆኑም አዕምሯቸው አልተሻሻለም ነበር።