በታንዛንያ አርግዘው የተገኙ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ታሰሩ

እርጉዝ ተማሪ Image copyright AFP

በደቡባዊ ታንዛኒያ ታንዳሂምባ በተሰኘ አካባቢ አምስት ተማሪዎች አርግዘው በመገኘታቸው ከነቤተሰባቸው መታሰራቸውና በመጨረሻ ግን በዋስ መለቀቃቸው ተሰማ።

የህፃናት መብት ተከራካሪዎች ደግሞ እርምጃው ያልተገባ ነው በማለት ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ናቸው። ታዳጊዎቹ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ሊታሰሩ የቻሉት በአካባቢው ኮሚሽነር ትእዛዝ ነበር።

የፆታ እኩልነትና የህፃናት መብት ተከራካሪዎች ህፃናቱ እንዲታሰሩ ትእዛዝ የሰጡ ሃላፊዎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው እያሉ ነው። ምክንያታቸው ደግሞ ሃላፊዎቹ ታዳጊዎቹን ያስረገዙ ወንዶችን ሳያስሩ ተጠቂዎቹን ለእስር መዳረጋቸው ነው።

ሞሃመድ አዚዝ የተባሉ አንድ የአካባቢው የመንግሥት ሃላፊ እንደገለፁት ታዳጊዎቹን ያስረገዙ ወንዶች እየተፈለጉ ነው።

ሃላፊው አዚዝ እንዳሉት ታዳጊዎቹ ከነወላጆቻቸው እንዲታሰሩ የተደረገው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው እየጨመረ ያለውን የታዳጊ ሴቶች እርግዝናን የመከላከል እርምጃ አካል ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለፈው ሁለት ዓመት ብቻ በአካባቢው 55 ተማሪዎች አርግዘዋል። ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ የፖለቲከኞችንም ትኩረት እየሳበ ነው።

ባለፈው ዓመት የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ የወለዱ ተማሪዎች ዳግም ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ መፈቀድ የለበትም የሚል አስተያየት በመስጠታቸው ትችቶች ተሰንዝረውባቸው ነበር።

የታዳጊዎች እርግዝና በደቡባዊ ታንዛኒያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ሲሆን የአገሪቱ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው በየዓመቱ በእርግዝና ምክንያት በርካታ ታዳጊዎች ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ።

የደቡብ ታንዛኒያ ክልል ኮሚሽነር ጊላሲየስ ባያንክዋ ለቢቢሲ እንደገለፁት ታዳጊዎቹም ላይ ሆነ ወላጆቻቸው ላይ ምንም አይነት ክስ አይመሰረትም።

በሌላ በኩል ደግሞ የታዳጊዎች እርግዝናን ለመከላከል ክልሎች ተገቢ ነው ያሉትን እርምጃ የመውሰድ ስልጣን እንዳላቸውም ሃላፊው ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች