ከኤርትራ ጋር የተፈጠረ ውጥረት የለም- ሱዳን

ከሰላ ሱዳን Image copyright Getty Images

ከኤርትራ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ ጦሯን ማሰማራቷን ተከትሎ በሁለቱ ሃገራት መካከል ውጥረት ነግሷል መባሉን ሱዳን አስተባብላለች።

የደቡብ-ምሥራቅ ካሳላ ግዛት አስተዳዳሪ እንደገለጹት ጦሩ የተሰማራው በአካባቢው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያን ለመቆጣጠር የተግባራዊ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም ነው።

እንደአስተዳዳሪው አዳም ጃማ ገለጻ ከሆነ በሱዳንና በኤርትራ መካከል ምንም ዓይነት ውጥረት የለም።

ባለፈው ሳምንት ሱዳን በምሥራቅ በሚገኘው ካሳላ እና በሰሜን ኮርዶፋን ለስድስት ወራት የሚዘልቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሕገ-ወጥ ጦር መሣሪያን ለመቆጣጠርና በዚህም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ንግድን ለመግታት የታለመ ነው ተብሏል።

እንደአዳም ጃማ ገለጻ ከሆነ በሺህዎች የሚቆጠሩ የሠራዊት አባላት በአካባቢው መሠማራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም እንጂ ከኤርትራ ጋር ውጥረት ስለመኖሩ የሚያሳይ አይደለም።

በማህበራዊ ሚዲያዎች የድንበር ላይ እንቅስቀሴው እንደተቋረጠ መገለጹን አስተባብለው፤ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት አለመቀየሩን አስታውቀዋል።

ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያንም ሆነ የሠዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አያስፈልግም በሚል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውሳኔውን ተችተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች