የኤርትራ ዘፈኖች በኢትዮጵያዊ አቀናባሪ

በረከት ወልዱ Image copyright Bereket

በረከት ወልዱ ወደ ሙዚቃ የገባበትን አጋጣሚ ሲያስታውስ "ከነጋዴ ቤተሰብ ስለተወለድኩ እኔም ነጋዴ ነበርኩኝ ሙዚቃ የኔ እኔ ደሞ የሙዚቃ አልነበርንም" ይላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር ተወልዶ ባደገባት አክሱም ከተማ ከሙዚቃ ጋር የተዋወቀው።

ለሁለት ወራት የሚቆይ የሙዚቃ ስልጥና የመሳተፍ ዕድልን ካገኘ በኋላ ነበር የበረከትና የሙዚቃ አብሮነት ተጠነሰሰ። የኑሮው አቅጣጫ ግን ከንግድ ወደ ጥበብ ሙሉ ለሙሉ አልተሽጋገረም። ሙሉ ጊዜውን ለሙዚቃ ሳይሰጥ የንግድ ሥራውን ቀጠለ።

በረከት ኑሮውን ከአክሱም ወደ አዲስ አበባ ሲቀይር ንግድና ሙዚቃም አብረውት ነበሩ። ለሙዚቃ ያለው ፍቅር ከፍ እያለ ሄዶ ጃዝ አምባ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቶ የሙዚቃ መሳርያ በመማር የተሻለ እውቀትና ችሎታ አገኘ።

በረከትና ኤርትራውያን ድምፃውያን

በረከት በ2005 ዓ.ም የራሱን ስቱድዮ በመክፈት የዘፋኖችን ድምፅ ከሙዚቃ መሳርያዎች ጋር ማቀናበር ጀመረ። አጭር በሚባል ጊዜ በርካታ ሥራዎችን በመስራት በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ እውቅናና ተቀባይነት ለማግኘት በቃ።

"በመድረክ የምሰራቸው ሥራዎችም ከሙዚቃ አፍቃሪዎች ጋር እንድተዋወቅ ረድተውኛል" የሚለው በረከት፤ አብሮ ለመስራት ይመኝ ከነበሩት ድምፃውያን ጋር የመሥራት እድልን እንዳገኘም ይናገራል። ለአብርሃም ገብረመድህንና ለሰለሞን ባይረ ተወዳጅ የዘፈን ቅንብሮች ለመስራትም ችሏል።

በትግርኛ ቋንቋ ከሚዘፍኑ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከታዋቂ ኤርትራዊያን ጋርም አብሮ እየሰራ ይገኛል። "ድምፃዊ ተስፋአለም ቆርጫጭ በቅርቡ 'አስመራ ወይ ዲሲ' በሚል ርዕስ ለህዝብ ያቀረበውን ሥራ አብረን ነው የሰራነው" ይላል በረከት።

ከእነዑስማን አብራር፣ ሮቤል ሚኪኤለ፣ ምሕረትአብ፣ ፍፁም ባራኪና ሌሎች በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ተወዳጅ የኤርትራ ድምፃውያን ጋር የሰራችው ሥራዎች እንዳሉም ያስረዳል።

ያቀናበራቸውን ዘፈኖች አጠናቆ ለባለቤቶቹ ሲያስረክብ ከፍተኛ እርካታ እንደሚሰማው ይሚናገረው በረከት፤ በውጭ ሃገር ሆነው የሚልኩለት ያላለቁ ማሳያ ሥራዎች ድምፃውያኑ በሚፈልጉትና በሚወዱት መንገድ አዘጋጅቶ ሲልክላችው ከድምፃውያኑም ሆነ ከሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ አድናቆት እንደሚቀርብለት ይገልፃል።

ድምፃዊ ሮቤል ሚኪኤለ ከበረከት ጋር አብረው ከሰሩ ኤርትራዊ ድምፃዊያን አንዱ ነው። "ከበረከት ጋር የተገናኘው ሙዚቃዬን የሚያቀናብርልኝ ሰው በምፈልግበት ጊዜ ነበር። በሥራው የሚደነቅ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ከገንዘብ ይልቅ ለሙዚቃ የሚጨነቅ ባለሙያ ነው" ሲል ያሞግሰዋል።

ለረጅም ጊዜ ከበረከት ጋር አብሮ የሰራው ድምፃዊ ሃይለ ገዙም "በረከት ለሞያው እንጂ ለገንዘብ የሚኖር አይደለም። በርካታ ቆንጆ ሥራዎች አብረን ሰርተናል። ሁሉም አንድ አይነት ቋንቋ በሚናገሩ ሁለት ህዝቦች ይደመጣሉ" ይላል።

Image copyright Bereket

ኢትዮጵያና ኤርትራ

"በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ሁኔታ ከሥራችን አላስተጓጎለንም" የሚለው በረከት በሁለቱም ሃገራት ያለው የትግርኛ ሙዚቃ ምትና ጣዕም ልዩነት እንደሌለው ያምናል።

"በጥንቃቄና ሙያዊ በሆነ ብቃት ከተሰራ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራ ትግርኛና ኤርትራ ውስጥ የሚሰራ የትግርኛ ዘፈን ልዩነት አይኖረውም" ይላል።

ከኤርትራዊያኑ ድምፃውያን ጋር በጥሩ መግባባትና መከባበር የሚሰራው በረከት "በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ቢፈታ ሙዚቃውን የበለጠ ለማሳደግ እድል ሊፈጥር ይችላል" ይላል።

በረከት አንድ ቀን በአካል ተቀራርቦ እየተወያዩ የትግርኛ ሙዚቃዎችን የመስራት ዕድል እንደሚኖር እምነት አለው።

ተያያዥ ርዕሶች