ሱዳን የዳቦ ዋጋ በመጨመርን በተቃወሙ ላይ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀች

sudan bread protest Image copyright Getty Images

የዱቄት ዋጋ መወደድን ተከትሎ በሱዳን የዳቦ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል። የሱዳን ባለስልጣናትም የዳቦ ዋጋ መጨመርን በማስመልከት የሚደረጉ ተቃውሞዎችን ለመበተን መንግሥት ኃይል እንደሚጠቀም በመግለፅ እያስጠነቀቁ ነው።

ባለፈው አርብ የሱዳን ዳቦ ቤቶች የዳቦ ዋጋን በእጥፍ ከፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ በመዲናዋ ካርቱምና በሌሎችም ከተሞች ተቃውሞ ተቀስቅሷል።

እስካሁን በተደረገው የአራት ቀናት ተቃውሞ ቢያንስ አንድ ሰው ሲገደል ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።

ተቃውሞውን ተከትሎ የሱዳን መንግሥት ለተቃውሞ የሚወጡትን የማሰር ዘመቻ ላይ ነው። ጉዳዩን በሚመለከት የሚዘግቡ መገናኛ ብዙሃን ላይም እርምጃ እየወሰደ ነው።

በተቃውሞ ምክንያት አንድ ተማሪ ሲሞት ሌሎች በመቁሰላቸው በምዕራብ ዳርፉር ትምህርት ተቋርጧል።

የሱዳን አገር ውስጥ ሚኒስትር ባቢኪር ዲግና ንብረት በማውደም ተቃውሟቸውን ለመግለፅ የሚሞክሩት ላይ የኃይል እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

ቢሆንም ግን ተቃውሞዎቹ ከዳቦ ዋጋ ጭማሪ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ክደዋል።

የዳቦ ዋጋ ጭማሪ ያሳየው ከሰባት የአሜሪካ ሳንቲም ወደ 14 ሳንቲም ነው። የዚህ ምክንያት ደግሞ መንግሥት የዱቄት ዋጋ ላይ የሦስት እጥፍ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ ነው።

ተቃዋሚዎችም ህዝቡ ይህን ድንገተኛ የሆነ ጭማሪና የኑሮ ውድነትን በመቃወም ወደ ጎዳና እንዲወጣ እየወተወቱ ነው።

በርካታ ተቃዋሚዎችም መታሰራቸው እየተነገረ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች